“አምላካችሁም አንድ አምላክ ብቻ
ነው፤ ከርሱ በቀር ሌላ አምላክ የለም፤ እርሱ እጅግ በጣም
ርኀሩኀ አዛኝ ነው፡፡” (አል-በቀራህ፡163)
አምላክ አንድ ብቻ መሆኑን አላህ ነግሮናል፡፡ ይህ
ማለት የሚመለከው አንድ ብቻ ነው ማለት ነው፡፡
ከአላህ ሌላ አምላክ ተደርጎ ሊይያዝ የሚገባው ነገር
የለም፡፡ ከርሱ ውጭ ማንም አይመለክም፡፡
በአላህ አምላክነት የማመን አስፈላጊነት፡-
በአላህ አምላክነት የማመን አስፈላጊነትን ከተለያዩ አቅጣጫዎች ግልፅ እንዲሆን ማድረግ፡-
1 ሰውም ሆነ ጋኔን የተፈጠረበት ዓላማ ነው፡፡ እነዚህ የተፈጠሩት አላህን በብቸኝነትና ያለምንም ተጋሪ ለመግገዛት
ነው፡፡ አላህም እንዲህ ብሏል…«ጋኔንና ሰውንም ሊግገዙኝ እንጅ ለሌላ አልፈጠርኳቸውም፡፡» (አል-ዛሪያት፡56)
2 የአላህ መልእክተኞች የተላኩት መለኮታዊ መፅሐፍት የወረዱት ለዚሁ ዓላማ ነው፡፡ ዓላማቸው በእውነት መመለክ
የሚገባው አላህ መሆኑን ለማፅናት ሲሆን ከርሱ ውጭ በሚመለኩ ነገሮች ደግሞ ለመካድ ነው፡፡ አላህ እንዲህ ብሏል…
“በየሕዝቡም ሁሉ ውስጥ አላህን ተገዙ፤ ጣዖትንም ራቁ በማለት መልእክተኛን በእርግጥ ልከናል፤” (አል-ነሕል፡36)
3 በሰው ልጅ ላይ የመጀመሪያው ግዴታ አላህን በብቸኝነት መገዛት ነው፡፡ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) ሙዓዝ ቢን
ጀበልን ወደ የመን ለሰበካ በላኩት ጊዜ ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነገር ነግረውት ነበር፡፡ እንዲህ ነበር ያሉት… “የመፅሐፍቱ
ባለቤት የሆኑ ህዝቦች ክርስቲያኖች /አይሁዶች/ ያጋጥሙሃል በመጀመሪያ ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚመለከ
አምላክ የለም ወደ ሚለው ቃል ጥራቸው፡፡” (አል-ቡኻሪ፡1389 ሙስሊም፡19)
ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ.) ለማለት የፈለጉት “በሁሉም የአምልኮ ዓይነቶች አላህን ብቻ አምልኩ በላቸው፡፡” ለማለት ነው፡፡
4 “ከአላህ በቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ የለም” የሚለው ቃል ትክክለኛ ትርጉም፥ በአላሀ አምላክነት ማመን
ነው፡፡ አምላክ ማለት የሚመለክ ማለት ነው፡፡ ከአላህ በቀር በዕውነት የሚመለክ የለም፡፡ ማንኛውም የአምልኮ ዓይነት
ከርሱ ውጭ ለማንም አናውልም፡፡
5 በአላህ አምላክነት ማመን፣ አዕምሮ የሚመራው አሳማኝ የሆነ፣ አላህ የሁሉ ነገር ፈጣሪ፣ ባለቤትና አዘጋጅ ነው
ብሎ የማመን ውጤት ነው፡፡
> አምልኮ ማለት ምን ማለት ነው?
> የአላህን ምንዳ መከጀል ዓላማ ያደረገ (ኒያ ያለው)
ማንኛውም ተግባር እንደ አምልኮ (ዒባዳ) የሚቆጠር ሲሆን፥
በዚህ ተግባርም ምንዳ (አጅር) ይገኝበታል፡፡
አምልኮ (ኢባዳ) ማለት፡- አላህ የሚወደውና
የሚደሰትበት እንዲሁም ንግግሮችንና ተግባራትን ሁሉ
የሚያጠቃልል ስም ሲሆን ሰዎች ይተገብሩት ዘንድ አላህ
ያዘዘው ተግባር ነው፡፡ ይህ ተግባር እንደ ሶላት፣ ዘካ፣
ሐጅ ግልፅ ሊሆን ይችላል፡፡ ወይም ደግሞ አላህንና
መልእክተኛውን (ሰ.ዐ.ወ.) እንደ መውደድ፣ አላህን
እንደ መፍራት፣ በርሱ እንደመመካትና ከርሱ እርዳታን
እንደመፈለግ ስውር ተግባር ሊሆን ይችላል፡፡ ሌሎችም
አንደዚሁ፡፡
በሁሉም የሀይወት ዘርፍ አላህን ስለማምለክ፡-
ወደ አላህ መቃረብን ዓላማው ያደረገ የማንኛውም አማኝ
ሙእሚን ተግባር በአምልኮ ዒባዳ ውሰጥ ይካተታል፡፡
በእስልምና ሃይማኖት መሠረት አምልኮ በሶላት፣
በፆምና በመሳሰሉ የፀሎት ስነ-ሥርዓቶች የተገደበ ነገር
አይደለም፡፡ ይልቁንም ማንኛውም ዓይነት ጠቃሚ
ተግባር መልካም የሆነን ዓላማ (ኒያ) እስካነገበ ድረስ፥
የአምልኮ ተግባር እንደሆነ የሚቆጠር ሲሆን ተግባሪውም
አላህ ዘንድ ይመነዳበታል፡፡
የአላሀ ትዕዛዝ በአግባቡ ለመፈፀም ይቻል ዘንድ
አካላዊ ጥንካሬ ለማግኘት በሚል ዓላማ አንድ
ሙስሊም ቢመገብ፣ ቢጠጣና ቢተኛ አላህ ዘንድ ምንዳ
ያገኝበታል፡፡
ስለዚህ ሙስሊም ህይወቱን በሙሉ ለአላህ እያስገዛ
ነው ማለት ነው፡፡ አላህን ለመታዘዝ ሰውነቱ ይጠነክር
ዘንድ ይመገባል፡፡ በዚህ ዓላማ በመመገቡ አላህን
እያመለከ ነው፡፡ ከአመንዝራነት ራሱን ለመጠበቅ
በሚል ዓላማ ትዳር ይመሰርታል፡፡ ጋብቻው በራሱ
የአምልኮ ተግባር ይሆንለታል፡፡ ልክ እንደዚሁ
ዓላማው ተመሳሳይ እስከሆነ ድረስ ንግዱ፣ ሥራው፣
ቢዝነሱ ሁሉ አምልኮ ይሆንለታል፡፡ እውቀት መፈለጉ፣
መመራመሩ፣ መፈላሰፉ፣ መፍጠሩ ሁሉ እንደ አምልኮ
ይቆጠርለታል፡፡
አንዲት እንስት ባልዋን፣ ልጆቿንና ቤቷን መንከባከቧ
በርሱ የአምልኮ ተግባር ይሆንላታል፡፡
በሁሉም የህይወት ዘርፍ የሚከናወኑ ጠቃሚ ተግባራት
በሙሉ መልካም ዓላማና ዕቅድን መነሻ አድርገው
እስከተፈፀሙ ድረስ እንደ አምልኮ ተግባር ይቆጠራሉ፡፡
አምልኮ (ዒባዳ) ሰው የተፈጠረበት ዓላማ ነው፡-
አላህ እንዲህ ይላል… “ጋኔንና ሰውንም ሊግገዙኝ
እንጅ ለሌላ አልፈጠርኳቸውም፡፡ ከነርሱም ምንም
ሲሳይ አልፈልግም፤ ሊመግቡኝም አልሻም፡፡ አላህ እርሱ
ሲሳይን ሰጪ የብርቱ ኃይል ባለቤት ነው፡፡” (አል-
ዛሪያት፡56-58)
አላህ ሰውንም ሆነ ጋኔን የፈጠረበት ጥበብ እርሱን
ይግገዙ ዘንድ እንደሆነ ተናግሯል፡፡ እነዚህ ፍጥረታት
አላህን የሚግገዙት ለራሳቸው ጥቅም እንጂ አላህ
ከእነርሱ ጥቅም ፈላጊ ሆኖ አይደለም፡፡
ሰው የተፈጠረበትን መለኮታዊ ይህን ዓላማ ዘንግቶ
በዓለማዊ ህይወት ውስጥ ሰጥሞ ከቀረ፥ በዚህ ምድር ላይ
ካሉ ሌሎች ፍጥረታት የሚለየው ምንም ነገር አይኖርም
ማለት ነው፡፡ እንስሳቶች ከሰው በተቃራኒ በቀጣዩ ዓለም
ስለሰሩት ሥራ አይጠየቁም እንጂ እነርሱም ይበላሉ፣
ይጠጣሉ፣ ይፈነጥዛሉ፡፡
አላህ እንዲህብሏል… “… እነዚያም የካዱት (በቅርቢቱ
ዓለም) ይጠቀማሉ፤ እንስሳዎችም እንደሚበሉ ይበላሉ
እሳትም ለነርሱ መኖሪያቸው ናት፡፡” (ሙሐመድ፡12)
ተግባርና ዓላማቸው ከእንስሳ ጋር
ተመሳስሏል፡፡ ነገርግን ከእንስሳ የሚለያቸው
በመጨረሻው ቀን የስራቸውን ውጤት
ማግኘታቸው ነው፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያትም
ምንም ከማያውቁት እንስሳት በተለየ አዕምሮ
ያላቸው፣ የሚገነዘቡና የሚያውቁ በመሆናቸው
ነው፡፡
የአምልኮ (ዒባዳ) መሠረቶት
አላህ እንተገብረው ዘንድ ያዘዘን አምልኮ በሁለት ዋና
ዋና መሠረቶች ላይ የተገነባ ነው፡-
አንደኛ፡- ሙሉ የሆነ ፍራቻና መተናነስ፡-
ሁለተኛ፡- ሙሉ የሆነ ውዴታን ለአላህ ማዋል፡-
አላህ በባሮቹ ላይ ግዴታ ያደረገው አምልኮ፥ ለአላህ
ብቻ የሚውል ሙሉ የሆነ ፍራቻ፣ መተናነስና ዝቅ
ማለትን በውስጡ ያካተተ ከመሆኑ ጎን ለጎን ሙሉ
የሆነ ውዴታና ክጃሎትን ለአላህ ብቻ ማዋልን
ይጠይቃል፡፡
ስለሆነም ልክ ምግብን ወይም ገንዘብን እንደምንወደው
ሁሉ አላህንም ፍራቻና መተናነስን ባላካተተ አኳኋን
የምንወደው ከሆነ አምልኮ አይባልም፡፡
ልክ እንደዚሁ አውሬና ጨቋኝ መንግስትን
እንደምንፈራው ሁሉ አላህንም ውዴታን ባላጎዳኘ
አኳኋን የምንፈራው ከሆነ ከአምልኮ አይቆጠርም፡፡
ሆኖም ግን በስራችን ውስጥ ውዴታንና ፍራቻን
ካቆራኘን ትክክለኛ አምልኮን አስገኝተናል፡፡ አምልኮ
ደግሞ ሊውል የሚገባው ለአላህ ብቻ ነው፡፡
የአምልኮ ቅድመ ሁኔታዎች፡-
አምልኮ የተስተካከለና አላህ ዘንድ ተቀባይነት
ያለው እንዲሆን ከተፈለገ ሁለት ቅድመ
ሁኔታዎችን ማሟላት ይኖርበታል፡፡
ሌላው ደግሞ
የአላህ መልእክተኛ
(ሰ.ዐ.ወ.) ከአከናወኑት
የአምልኮ ተግባር
ጋር የሚጣጣምና
የሚስማማ መሆን
ይኖርበታል፡፡
የመጀመሪያው አምልኮን
ያለ ምንም ተጋሪ ለአላሀ
ብቻ ማዋል ሲሆን
አላህ እንዲህ ብሏል “አይደለም እርሱ በጎ ሰሪ ሆኖ ፊቱን
ለአላህ የሰጠ ሰው ለርሱ በጌታው ዘንድ ምንዳው አለው፤
በነርሱም ላይ ፍርሃት የለባቸውም እነሱም አያዝኑም፡፡”
(አል-በቀራህ፡112)
በዚህ አንቀፅ ውስጥ “ፊቱን ለአላህ የሰጠ ሰው” ማለት፥
የአላህን አንድነት በተግባር ያረጋገጠና አምልኮን ለርሱ ብቻ
ያጠራ ማለት ነው፡፡
“በጎ ሰሪ ሆኖ” የሚለው ደግሞ፥ የአላህን ህግና
የመልእክተኛውን (ሰ.ዐ.ወ.) አርዓያነት የሚከተል ማለት
ነው፡፡
ሥራን ከመልእክተኛው (ሰ.ዐ.ወ.) ሱንና
(መንገድ) ጋር ማጣጣም ማለት እንደ ሶላት፣
ፆምና አላህን ማውሳት የመሳሰሉት ተግባራትን
እርሳቸው ባከናወኑት መሠረት መፈፀም ማለት ነው፡፡
ነገር ግን ሌሎች የዕለት ተዕለት ተግባራትን
ለጥሩ ዓላማ (ኒያ) እስካከናወናቸው ድረስ
ከአምልኮ ተግባራት ተርታ የሚመደቡ ቢሆንም፥
ከአላህ መልእክተኛ ሱንና ጋር የግድ እንዲጣጣሙ
ማድረግ አይጠበቅብንም፡፡ ባይሆን መጠንቀቅ
የሚኖርብን ሸሪዓውን የሚቃረን ሐራም ነገር ላይ
ላለመውደቅ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው የአላህን
ትዕዛዝ ለመተግበር ጠንካራ ያደርገው ዘንድ
ስፖርት ቢሰራ ወይም የቤተሰቡንና የልጆቹን
ወጪ ለመሸፈን ስራ ቢሰራ ኒያውን እስካሳመረ
ድረስ እንደ አምልኮ ተግባር ቢቆጠርለትም ከሱንና
ጋር እንዲጣጣም ማድረግ ግዴታ አይደለም፡፡
> ሺርክ (የአምልኮ ተግባርን ከአላህ ዉጪ) ላለ አካል ማጋራት
• ሺርክ በአላህ አምላክነት ላይ ያለንን እምነት
የሚፃረር ነገር ነው፡፡ በአላህ አምላክነት ማመንና
የአምልኮ ተግባራትን ለርሱ ብቻ ማዋል ከታላላቅና
ወሳኝ ከሆኑ ግዴተዎች ውስጥ ግንባር ቀደሙ
መሆኑ እርግጥ ከሆነ፥ ከዚህ በተመሳሳይ መልኩ
ለአላህ ብቻ የሚገባውን የአምልኮ ተግባር ለሌላ
አካል ማጋራት ደግሞ አላህ ዘንድ የወንጀሎች ሁሉ
ቁንጮ ነው፡፡ ንሰሃ ካልገቡ በቀር አላህ በፍፁም
የማይምረው ብቸኛ ወንጀል ነው፡፡
አላህ እንዲህ ይላል… “አላህ በርሱ ማጋራትን
በፍፁም አይምርም፤ ከዚህ ሌላ ያለውንም ኀጢአት
ለሚሻው ሰው ይምራል፡፡ በአላህም የሚያጋራ ሰው
ታላቅን ኃጢአት በእርግጥ ቀጠፈ፡፡” (አል-ኒሳእ፡
48)
ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ.) አላህ ዘንድ ከወንጀሎች ሁሉ ታላቁ
ምን እንደሆነ ሲጠየቁ “አላህ ፈጥሮህ ሳለ ለርሱ
ተጋሪ ማድረግህ ነው” በማለት መልሰዋል፡፡ (አል-
ቡኻሪ፡ 4207 / ሙስሊም፡ 86)
• በአላህ ማጋራት ስራን በሙሉ ከንቱና ውድቅ
ያደርጋል፡፡ አላህም እንዲህ ብሏል፡፡ … “…ባጋሩም
ኖሮ ይሠሩት የነበሩት ከነርሱ በታበሰ ነበር፡፡” (አል-
አንዓም፡88)
በአላህ አጋርቶ ንሰሃ ሳይገባ የሞተ ሰው
ዕጣፈንታው ዘላለም በጀሃነም እሳት መቀጣት
ይሆናል፡፡ አላህ እንዲህ ብሏል፡፡ …”እነሆ! በአላህ
የሚያጋራ ሰው አላህ በርሱ ገነትን በእርግጥ እርም
አደረገ፤ መኖሪያውም እሳት ናት፤ ለበዳዮችም ምንም
ረዳቶች የሏቸውም፡፡” (አል-ማኢዳህ፡72)
ሺርክ ሁለት ዓይነት ናቸው፡፡ ታላቅና ታናሽ
ታላቁ ሺርክ፡- ይህ ማለት አንድን የአምልኮ
(ዒባዳ) ዓይነት ከአላህ ውጪ ላለ አካል
አሳልፎ መስጠት ማለት ነው፡፡ አንድ አላህ
የሚወደውን ንግግርም ሆነ ተግባር ለአላህ
ብቻ ካዋልነው አንድነቱን አፀደቅን ወይም
አመንበት ማለት ነው፡፡ ይህን ተግባር ከርሱ
ሌላ ለሆነ አካል ካዋልነው ደግሞ፥ ክደነዋል
አጋርተንበታል፡፡
ለእንዲህ ዓይነቱ የሺርክ ተግባር ምሳሌን መጥቀስ
እንችላለን፡፡ ከአላህ ውጪ ያን አካል ከህመም
እንዲያሽረን፣ ሲሳይን እንዲያሰፋልን ከጠየቅነውና
ከለመንነው በታላቁ የሺርክ ተግባር ላይ ወድቀናል
ማለት ነው፡፡ ከአላህ ውጪ ለሆነ ነገር ብንሰግድ ወይም
በርሱ ላይ ብንመካም እንደዚያው ነው፡፡
አላህ እንዲህ ይላል … “ጌታችሁም አለ፡- ለምኑኝ
እቀበላችኋለሁና፤ እነዚያ እኔን ከመገዛት የሚኮሩት
ተዋራጆች ሆነው ገሃነምን በእርግጥ ይገባሉ፡፡” (አል-
ሙእሚን፡60)
እንዲህም ይላል … “… ምእምናንም እንደ ሆናችሁ በአላህ
ላይ ተመኩ አሉ፡፡” (አል-ማኢዳህ፡23)
ሌላ ሱራ ላይም እንዲህ ብሏል…”ለአላህም ስገዱ
ተገዙትም፡፡” (አል ነጅመ፡ 62)
እነዚህን ተግባራት ከአላህ ሌላ ላለ አካል ያዋለ ሰው
አጋሪ እንዲሁም ከሃዲ ይሆናል፡፡
ትንሹ ሺርክ፡- ይህ ደግሞ ወደ ታላቁ ሺርክ
ሊያደርስ የሚችል ንግግር ወይም ተግባር
ነው፡፡ ትንሹ ሺርክ ታላቁ ሺርክ ላይ ሊጥል
ይችላል፡፡
ለዚህኛው የሚሆን ምሳሌ መጥቀስም ይቻላል፡-
ሰው አንዲያይለት በማሰብ ሶላትን ማስረዘም ወይም
ሰዎች እንዲያደንቁት በማሰብ ቁርኣን ሲያነብ ወይም
አላህን ሲዘክር ድምፁን ከፍ ማድረገና የመሳሰሉትን
መጥቀስ ይቻላል፡፡ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) “እኔ
ለእናንተ በጣም ከምፈራላችሁ ነገር ውስጥ አንዱ
ትንሹ ሺርክ ነው፡፡” በማለት ሲናገሩ ሰሃቦችም “አንቱ
የአላህ መልእክተኛ ትንሹ ሺርክ ምንድ ነው?” በማለት
ጠየቋቸው፡፡ እርሳቸውም “የይዩልኝ ስራ ነው፡፡”
በማለት መልስ ሰጡ (አህመድ፡2363)
ሆኖም ግን ፍፁም ለሰው ተብሎ የሚደረግ
የአምልኮ ተግባር ሶላትም ሆነ ፆም የመናፍቅ
ሥራ ነው፡፡ እንዲህ ያለው ተግባር
ከእስልምና ሃይማኖት ውጪ የሚያደርግ
ታላቅ የሺርክ ተግባር ነው፡፡
ከሰው መፈለግና ሰውን አንዳንድ ነገር
መጠየቅ የሺርክ ተግባር ነውን?
የእስልምና ሃይማኖት የተደነገገው የሰውን
አዕምሮ ከንቱ ከሆኑ እምነቶች ነፃ ለማውጣት
ነው፡፡ የተደነገገው የሰው ልጅ ከአላህ ውጪ
ላለ አካል ዝቅ እንዳይል ነው፡፡
ለሙታንም ሆነ ግዑዝ ለሆኑ አካላት ዝቅ
ብሎ በመተናነስ ፍላጎትን መጠየቅ ህገ-ወጥ
የሆነ ተግባር ነው፡፡ ይህ ከንቱ እምነትና
ሺርክ ነው፡፡
ነገር ግን አጠገባችን ያለንና ህይወት
ያለውን ሰው አቅሙ የሚችለውን ነገር
እንዲያደርግልን ብንጠይቀው ወንጀል
አይደለም፡፡ ለምሳሌ ውሃ ውስጥ የሰጠመ
ሰው ህይወቱን ያተርፈው ዘንድ ሰውን
መጠየቁ፣ ወይም አንድ ሰው ዱዓእ
እንዲያደርግልን ብንጠይቅ እስልምና
የሚፈቅደው ህጋዊ ተግባር ነው፡፡
> በህይወት ያለና አጠገባችን የሆነን ሰው አቅሙ የሚፈቅደውን ነገር
እንዲያደርግልን ብንጠይቀው፥ እንደ የዕለት ውሎ የሚቆጠር ህጋዊ የሆነ
ተግባር ነው፡፡
ሙታንን ወይም ግዑዝ አካላትን መከጀልና መማፀን የሺርክ ተግባር ነውን?
ከሕያው ሰው እርሱ የማይችለውን ነገር ከርሱ መፈለግ ወይም መከጀል ማለት አንድ
መውለድ የማይችል መካን፣ ከሕያው ሰው ፃድቅ ልጅ እንዲሰጠው እንደመለመን ነው፡፡
ይህ ደግሞ ከኢስላም ጋር የሚቃረን ትልቁ የማጋራት ተግባር ነው፡፡ ምክንያቱም ከአላህ
ሌላ ያለን አካል መለመን ነውና፡፡
ሕያው ሆኖ ጥያቄህንና ልመናህን ሊሰማ የሚችልን አካል መለመንህና መጠየቅህ፡፡
እርሱ በሚችለው ነገር ላይ እንዲረዳህና እንዲያግዝህ በጠየቅከው ዓይነት? ልመናህን
ለመመለስና ጥያቄህን ለመስማት ይችላልን?
ይህ ›=eLUንና ኢማንን የሚቃረን ነው፡፡ ምክንያቱም
ሙታንና ግዑዛን ነገሮች፣ ጥያቄውን መስማትም ሆነ
ምላሽ መስጠት አይችሉም፡፡ ልመና (ዱዓ) አምልኮ ነው።
በመሆኑም ከአላህ ሌላ ለሆነ አካል አሳልፎ መስጠት
ማጋራት ነው፡፡ ›=eLU በታወጀበት ዘመን የነበሩ ዐረቦች
ያጋሩ የነበሩት ግዑዛንንና ሙታንን በመለመን ነበር፡፡
ይህ ተገቢ ልመና ነው፡፡ ምንም ችግር የለውም፡፡
በሰዎች ማህበራዊ ግንኙነትና የዕለት ተዕለት ሕይወት
ውስጥ ከሚከሰቱ ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው፡፡
አይቻልም(በፍፁም) አዎን
አይቻልም(በፍፁም) አዎን
> በአላህ ስሞችና ባህሪያት ማመን፡-
ይህ ማለት፥ አላህ በመፅሐፉ ውስጥ ወይም
መልእክተኛው በስሱናቸው ያፀደቁትንና አላህ እራሱን
የሰየመበትን ስም እንዲሁም ማንነቱን የገለፀበትን ባህሪ
ለአላህ በሚገባው መልኩ ማመን ማለት ነው፡፡
ከጉድለት የጠራ የሆነው አላህ ምርጥ የሆኑ ስሞችና
ሙሉዕ የሆኑ ባህሪያት አሉት፡፡ በስሙም ሆነ በባህሪያቱ
ፍፁም አምሳያ የሌለው ጌታ ነው፡፡ እንዲህ ይለናል
“የሚመስለው ምንም ነገር የለም እርሱም ሰሚው
ተመልካቱ ነው፡፡” (አል-ሹራ፥11)
አላህ በሁሉም ስሞቹና ባህሪያቱ ከየትኛውም ፍጡር
ጋር ፍፁም የማይመሳሰልና የጠራ ነው፡፡
ከአላህ ስሞች ውስጥ የተወሰኑት፡-
አላህ እንዲህ ይላል “እጅግ በጣም ርኀሩኀ በጣም አዛኝ”
(አል-ፋቲሐህ፡3)
አላህ እንዲህ ይላል “እርሱም ሰሚው ተመልካቹ
ነው፡፡” (አል ሹራ፡11)(አል ሹራ 11)
አላህ እንዲህ ይላል “እርሱም አሸናፊው ጥበበኛው
ነው፡፡” (ሉቅማን፡9)
አላህ እንዲህ ይላል “አላህ ከርሱ በቀር ሌላ አምላከ
የለም፤ ሕያው ራሱን ቻይ ነው፤” (አል-በቀራህ፡ 255)
አላህ እንዲህ ይላል “ምስጋና ለአላህ ይገባው የዓለማት
ጌታ ለሆነው፡፡” (አል-ፋቲሐህ፡2)
ኃያሉ አላህን ያሳውቀናል፡- በአላህ ስሞችና ባህሪያት ያመነ ሰው ስለ አላህ ያለው እውቀት ይጨምራል፡፡
በአላህ ላይ ያለው እርግጠኛ እምነትም ይጨምራል፡፡ ስለ አላህ አንድነት ያለው ዕምነት ይጠነክራል፡፡ የአላህን
ስሞችና ባህሪያት ያወቀ ሰው፥ ቀልቡ በአላህ ታላቅነት፣ ውዴታና አክብሮት መሞላቱ የግድ ነው፡፡
አላህን በስሞቹ ማወደስ እንችላለን፡፡ ይህ ምርጥ ከሆኑ የዚክር (የውዳሴ) ዓይነቶች ውስጥ ይካተታል፡፡ አላህ
እንዲህ ይላል… “እናንተ ያመናችሁ ሆይ! አላህን ብዙ ማውሳትን አውሱት፡፡” (አል-አሕዛብ፡ 41)
ስምና ባህሪውን ካወቅን፥ በስሞቹና በባህሪያቱ ልንማፀነው አንችላለን፡፡ አላህ እንዲህ ይላል “ለአላህም
መልካም ስሞች አሉት ስትፀልዩም በርሷም ጥሩት” (አል-አዕራፍ፡ 180)በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፡- አንተ
ሲሳይን ሰጪ ሆይ! ሲሳይን ስጠኝ፡፡ አንተ ይቅር ባይ ሆይ! ይቅር በለኝ፡፡ አንተ አዛኝ ሆይ! እዘንልኝ…
ማለት እንችላለን፡፡
በአላህ ስሞችና ባህሪያት የማመን ፍሬዎች፡-
ከፍ ያሉ የእምነት ደረጃዎች፡-
እምነት የተለየዩ ደረጃዎች አሉት፡፡ የአንድ ሙስሊም እምነት መዘንጋቱንና ሐጢአቱን መነሻ አድርጎ ሊቀንስ
ይችላል፡፡ ልክ እንደዚሁ ለአላህ ባለው ታዛዥነት፣ አምልኮና ፍራቻ ልክ እምነቱ ይጨምራል፡፡
የእምነት ከፍተኛው ደረጃ ሸሪዓው እንዳለው «ኢህሣን» በሚል ይተወቃል፡፡ ስለ «ኢህሣን» ምንነት ነቢዩ
(ሰ.ዐ.ወ.) እንዲህ ሲሉ ገልፀውታል… “አንተ ባታየው እንኳ እርሱ ያይሃልና፥ አላህን ስትገዛው እያየኸው
እንደምትገዛው ሆነህ ተገዛው፡፡” (አል-ቡኻሪ፡50 ሙስሊም፡8)
ቆመህም ሆነ ተቀምጠህ፣ በደስታም ሆነ በሃዘን
ወቅት በአጠቃላይ በሁሉም ሁኔታ ውስጥ ሆነህ
አላህን ማስታወስ ይኖርብሃል፡፡ አላህ ምንግዜም
በቅርበት ይመለከትሃል፡፡ እየተመለከተህ መሆኑን
ካወቅህ ወንጀል አትፈፅምም፡፡ እርሱ ካንተ ጋር
መሆኑን የምታውቅ ከሆነ ፍርሃትም ሆነ ተስፋ
መቁረጥ አይቆጣጠሩህም፡፡ በእርግጥ አላህን
በሶላትህና በዱዓህ አያናገርከው ብቸኝነት
ሊሰማህ አይችልም፡፡
የሰወርከውንም ግልፅ ያደረግከውንም
አላህ እንደሚየውቅ እየተገነዘብክ ነፍስህ
ወደ ኃጢአት ልትገፋፋህ አትችልም፡
፡ኃጢአት ላይ ተዳልጠህና ተሳስተህ
ከወደቅህ ደግሞ ወደ አላህ በመመለስ
ምህረቱን ትማፀነዋለህ እርሱም ይምርሃል፡፡
አላህ ክፉ ነገሮችን ሁሉ ለምእመናን ይከላከልላቸዋል፡፡ ከጭንቅ ያድናቸዋል፡፡ ከጠላቶቻቸው ሴራም
ይጠብቃቸዋል፡፡ አላሀ እንዲህ ይላል “አላህ ከነዚያ ካመኑት ላይ ይከላከልላቸዋል፡፡” (አል-ሐጅ ፡ 38)
በአላህ ላይ የሚኖረን እምነት መልካም የሆነን ህይወት፣ ደስታንና ፍስሃን ያጎናፅፋል፡፡ አላህ እንዲህ
ይላል … “ከወንድ ወይም ከሴት እርሱ አማኝ ሆኖ በጎን የሠራ መልካም ኑሮን በእርግጥ እናኖረዋለን፤”
(አል-ነሕል፡97)
እምነት ነፍስን ከከንቱ እምነቶች ፅዱ እንዲሆን ያደርጋል፡፡ በአላህ የሚያምን ሰው፥ ጉዳዩን ሁሉ ለአንድ
አላህ ብቻ ይተዋል፡፡ እርሱ የዓለማት ጌታ ነው፡፡ እርሱ እውነተኛ አምላክ ነው፡፡ ከርሱ ሌላ እውነተኛ
አምላክ የለም፡፡ በአላህ የሚያምን ሰው ፍጡርን አይፈራም፡፡ ማንንም ሰው በቀልቡ አይከጅልም፡፡
ከዚህም በላይ ከንቱና አላስፈላጊ ከሆኑ እምነቶች ራሱን ነፃ ያደርጋል፡፡
የኢማን ከፍተኛ ተፅዕኖ፡- የአላህን ውዴታ ያስገኛል፡፡ ጀነት ያስገባል፡፡ ቋሚና ዘላለማዊ ለሆነ የፀጋ ስኬት
ያበቃል፡፡ ሙሉ የአላህ እዝነትን ያስገኛል፡፡
አላህን የማመን ፍሬዎች፡-
> በመላእክት ማመን
በመላእክት የማመን ትርጓሜ
ይህ የመላእክትን መኖር፣ እነርሱ ከሰው
ዘርም ከአጋን”ትም ዓለም ያልሆኑ የስውር
ዓለም ፍጡራን እንደሆኑ በቁርጠኝነት
ማጽደቅ ነው፡፡ እነርሱ የተከበሩና አላህን
ፈሪዎች ናቸው፡፡ አላህን ትክክለኛ የሆነ
መገዛትን ይገዙታል፡፡ እርሱ ያዘዛቸውን
በመፈፀም ያስተናብራሉ፡፡ በአላህ ላይ
ፈፅሞ አያምጹም፡፡
አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡-
«(መላእክት) የተከበሩ ባሮች ናቸው፡
፡ በንግግር አይቀድሙትም (ያላለውን
አይሉም) እነሱም በትዕዛዙ ይሰራሉ፡፡»
(አል አንቢያ 26-27)
በእነሱ ማመን ከኢማን ስድስት መሠረቶች
አንዱ መረት ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ
ብሏል፡- «መልክተኛው ከጌታው ወደርሱ
በተወረደው አመነ፡ ምዕመናኖችም
(እንደዚሁ) ሁሉም በአላህ በመላእክቱም
በመጻሕፍትቱም በመልክተኞቹም….
አመኑ፡፡» (አል በቀራ 285)
ኢማንን አስመልክተው ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ)
እንዲህ ብለዋል፡ «በአላህ፣ በመላእክቱ፣
በመጽሐፍት፣ በመልዕክተኞች፣
በመጨረሻው ቀንና በክፉም በደጉም
በአላህ ውሳኔ ልታምን ነው፡፡»
(ሙስሊም 8)
በመላእክት ማመን ምንን ያካትታል?
በመኖራቸው ማመን፡ እነርሱ የአላህ ፍጥረታት እንደሆኑ
እናምናለን፡፡ በተጨባጭ ያሉ ናቸው፡፡ አላህ የፈጠራቸው
ከብርሃን ነው፡፡ እርሱን በመገዛትና በመታዘዝ ላይ አግርቷቸዋል፡፡
ከነርሱ መካከል እንደ ጂብሪል (ዐ.ሰ) በስሙ ያወቅነውን
እስከነስሙ እናምናለን፡፡ በስማቸው ያላወቅነውናቸውንም
በጥቅሉ እናምንባቸዋለን፡፡
ከባህሪያቸው በምናውቀው ማመን፡፡ ከባህሪያቸው መካከል፡
• እነርሱ የስውር ዓለም ፍጥረታት መሆናቸው፡፡ ለአላህ የሚገዙ
ፍጡራን ናቸው፡፡ ከቶም የጌትነትም ሆነ የአምላክነት ባህሪ
የላቸውም፡፡ እንደውም እነሱ አላህን ለመታዘዝ ሙሉ በሙሉ
የተገሩ የአላህ ባሮች ናቸው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡-
«አላህ ያዘዛቸውን በመጣስ አያምጡም፡፡ የሚታዘዙትንም ሁሉ
ይሰራሉ፡፡» (አል ተህሪም 6)
• የተፈጠሩት ከብርሃን ነው፡፡ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡
«መላእክት ከብርሃን ተፈጠሩ፡፡» ሙስሊም 2996
• ክንፎች አሏቸው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) ለመላእክት ክንፍን እንዳደረገ
ተናግሯል፡፡ የክንፎቻቸው ብዛት ይበላለጣል፡፡ አላህ (ሱ.ወ)
እንዲህ ብሏል፡- «ምስጋና ሰማያትንና ምድርን ፈጣሪ፣ መላእክትን
ባለ ሁለት ሁለት፣ ባለ ሦስት ሦስትም፣ ባለ አራት አራትም
ክንፎች የኾኑ መልክተኞች አድራጊ ለኾነው አላህ ይገባው፤
በፍጥረቱ ውስጥ የሚሻውን ይጨምራል፤ አላህ በነገሩ ሁሉ ላይ
ቻይ ነውና፡፡» (ፋጢር 1)
በአላህ ትዕዛዝ መሰረት እነርሱ ከሚያከናውኗቸው ስራዎቻቸው ባወቅነው ማመን፡፡ ከነርሱ መካከል፡- 4
• መለኮታዊ ራዕይን ወደ መልክተኞች በማምጣት የተወከለ አለ፡፡ እሱም ጂብሪል (ዐ.ሰ) ነው፡፡
• ነፍስን በማውጣት የተወከለም አለ፡፡ እርሱም የሞት መልአክና ተባባሪዎቹ ናቸው፡፡
• መልካምም ሆነ እኩይ፣ የባሮችን ስራ መዝግቦ በማቆየት ወይም በመጠበቅ የተወከሉ አሉ፡፡ እነሱም የተከበሩ
ፀሐፍት መላእክት ናቸው፡፡
የአላህን ልቅና፣ ኃይል፣ ሙሉዕነትና ችሎታ ያሳውቃል፡፡ የፍጥረታት ትልቅነት የፈጣሪያቸውን
ትልቅነት ያሳያል፡፡ በመሆኑም አንድ ሙዕሚን በመላእክት በማመኑ ለአላህ የሚሰጠው ደረጃና ለርሱ
ያለው ከበሬታ ይጨምራል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) ብዙ ክንፎች ያሏቸው መላዕክትን ከብርሃን የፈጠረ ነው፡፡
አላህን በመታዘዝ ላይ ጽናትን ያጎናጽፋል፡፡ መላዕክት ስራዎቹን በሙሉ እንደሚፅፉ የሚያምን ሰው፣
ይህ እምነቱ የአላህ ፍራቻ እንዲያድርበት ያደርጋል፡፡ በይፋም ሆነ በድብቅ በአላህ ላይ አያምጽም፡፡
አንድ አማኝ በዚህ ሰፊ ዓለም ውስጥ አላህን የሚታዘዙ መላእክት አብረውት በተሟላና ባማረ መልኩ
እንዳሉ በእርግጠኝነት በሚረዳ ጊዜ አላህን የመታዘዝ ትዕግስትን ይላበሳል፡፡ መላመድንና መረጋጋትን
ያገኛል፡፡
ከመላእክት መካከል የሚጠብቋቸውና የሚከላከሉላቸው በማድረግ አላህ ለአደም ልጆች በቸረው
ትኩረቱና ክትትሉ ማመሰገን፡፡
በመላእክት የማመን ፍሬ ወይም ጥቅም፡፡
በመላእክት ማመን በሙእሚን ሕይወት ውስጥ ትልቅ ጥቅም አለው፡፡ ከነኚህ ጥቅሞች መካከል የሚከተሉትን
እንጠቅሳለን፡፡
> ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ሰማይ በውስጧ ባሉት ፍጥረታት እንደተጨናነቀች ተናግረዋል፡፡ በውስጧ
የስንዝር ያክል ቦታ እንኳን ቢሆን የቆመ ወይም ያጎነበሰ፣ ሩኩዕ ያደረገ ወይም በግንባሩ የተደፋ፣
ሱጁድ ያደረገ መልኣክ ቢኖር እንጂ ክፍት እንደማይሆን ተናግረዋል፡፡
> በመጽሕፍት ማመን
> የተከበረውን ቁርኣን መፃፍ የሚከናወነው
ረቀቅ ባሉ ስርዓቶች መሰረት፣ በብቃትና
በጥራት ነው፡፡
በመጽሐፍት የማመን ትርጓሜ
አላህ (ሱ.ወ) በመልክተኞቹ ላይ ወደ ባሮቹ ያወረዳቸው
መጽሐፍት እንዳለው፣ እነኚህ መጽሐፍት በሙሉ
የአላህ ቃልና ንግግር እንደሆኑ ማመን ነው፡፡ ለክብርና
ልቅናው ተገቢ በሆነ መልኩ በርግጥ ተናግሯል፡፡ እነኚህ
መጽሐፍት በውስጣቸው ለሰው ልጅ፣ ለሁለቱም ዓለም
የሚሆን መመሪያና ብርሃን የያዙ እውነቶች ናቸው
ማለትን በቁርጠኝነት ማረጋገጥ፡፡
በመጽሐፍት ማመን ከኢማን ማዕዘናት መካከል አንዱ
ማዕዘን ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «እናንተ
ያመናችሁ ሆይ! በአላህና በመልክተኛው፣ በዚያም
በመልክተኛው ላይ ባወረደው መጽሐፍ፣ በዚያም
ከበፊቱ ባወረደው መጽሐፍ እመኑ፡፡» (አል ኒሳእ 136)
አላህ (ሱ.ወ) በርሱ በመልዕክተኛው ላይ ባወረደው
መጽሐፍ፣ በቁርኣን እንድናምን አዟል፡፡ ከቁርኣን በፊት
በተወረዱ መጽሐፍት ማመንን አዟል፡፡
ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ኢማንን አስመልክተው እንዲህ ብለዋል፡
- «በአላህ፣ በመላእክቱ፣ በመጽሐፍቱ፣ በመልዕክተኞቹ፣
በመጨረሻው ቀንና በክፉም በደጉም በአላህ ውሳኔ
ልታምን ነው፡፡» (ሙስሊም 8)
የቁርኣን ልዩ መገለጫዎች
የተከበረው ቁርኣን በነብያችንና በአርአያችን በሙሐመድ
(ሰ.ዐ.ወ) ላይ የተወረደ የአላህ ቃል ነው፡፡ በመሆኑም
ሙእሚን ይህን” መጽሐፍ በእጅጉ ያልቀዋል፡፡ ድንጋጌዎቹን
ለመተግበርና አንቀፆቹን እያስተነተነ ለማንበብ ይጥራል፡፡
ይህ ቁርኣን በቅርቢቱ ዓለም መመሪያችን፣ በመጨረሻው
ዓለም የስኬታችን ሰበብ መሆኑ ብቻ ልዩ ለመሆን
ይበቃዋል፡፡
የተከበረው ቁርኣን በርካታ መለያዎች አሉት፡፡
ከቀደሙት መለኮታዊ መጽሐፍት የሚነጥሉት የርሱ ብቻ
የሆኑ የተለያዩ መገለጫዎችም አሉት፡፡ ከነኚህም መካከል፡-
የተከበረው ቁርኣን የአምላክን ድንጋጌ ማጠቃለያ
የያዘ መሆኑ፡፡ በቀደምት መጽሐፍት ውስጥ
ያለውን፣ አላህን በብቸኝነት የመገዛት ትዕዛዝን
የሚያጠናክር ኾኖ ነው የመጣው፡፡
አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «ወደ አንተም
መጽሐፉን ከበፊቱ ያለውን መጽሐፍ አረጋጋጭና
በርሱ ላይ ተጠባባቂ ሲኾን በውነት አወረድን»
(አል ማኢዳ 48)
በመጽሕፍት ማመን ምንን ያካትታል?
ከአላህ በትክክል የተወረዱ በመሆናቸው
ማመን
የአላህ ቃል (ንግግር) መሆናቸውን ማመን
በነብያችን (ሰ.ዐ.ወ) ላይ እንደተወረደው
ቁርኣን፣ በሙሳ(ዐ.ሰ) ላይ እንተወረደው
ተውራት፣ በዒሳ(ዐ.ሰ) ላይ እንደተወረደው
ኢንጂል ዓይነት አላህ በስም የጠራቸውን
በስማቸው ማመን፡፡
ከዜናዎቻቸው፣ በትክክለኛ ዘገባ የደረሱንን
በእውነተኝነታቸው ማመን፡፡
«ከበፊቱ ያለውን መጽሐፍ አረጋጋጭ» ማለት በቀደምት መጽሐፍት ውስጥ ከተነገሩ ዜናዎች፣ ከተላለፉ የእምነት
አመለካከቶችና ጉዳዮች ጋር የሚስማማና የማይቃረን ማለት ነው፡፡ «በርሱ ላይ ተጠባባቂ» የሚለው ደግሞ ከርሱ
በፊት የነበሩ መጽሐት ላይ የሚመሰክርና በአደራ የሚጠብቅ ማለት ነው፡፡
እነሆ የሰው ልጆች በሙሉ በቋንቋና በጎሳ መለያየታቸው እንዳለ ሆኖ፣ ዘመናቸው ምንም እንኳ ከቁርኣን መወረድ
በኋላ የመጣ ቢሆንም እርሱን የመከተል፣ እርሱ ያቀፈውን የመተግበር ግዴታ አለባቸው፡፡ ቀደምት መጽሐፍት
ግን የተወረዱት ከዚህ ተቃራኒ በሆነ መልኩ ለተወሰኑ ሕዝቦችና በተወሰነ ዘመን ላይ ነበር፡፡ አላህ(ሱ.ወ) እንዲህ
ብሏል፡- «ይህም ቁርኣን እናንተንና የደረሰውን ሰው ሁሉ በርሱ ላስፈራራበት ወደኔ ተወረደ (በል)፡፡» (አል
አንዓም 19)
አላህ (ሱ.ወ) የተከበረውን ቁርኣን የመጠበቁን ኃላፊነት ለራሱ አድርጎታል፡፡ በመሆኑም የመቀየር፣ የመደለዝ፣
የመከለስና የመበረዝ እጅ አልተሰነዘረበትም፡፡ ወደፊትም ለመቼውም አይዘረጋበትም፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ
ብሏል፡- «እኛ ቁርኣንን እኛው አወረድነው፤ እኛም ለርሱ ጠባቂዎቹ ነን፡፡» (አል ሒጅር 9)
ሰለሆነም በውስጡ ያሉ ዜናዎች በሙሉ ትክክለኛ ናቸው፡፡ ልንቀበለውም የግድ ይላል፡፡
ቁርኣንን አስመልክቶ ያለብን ግዴታ ምንድን ነው?
• ቁርኣንን ልንወድ ይገባል፡፡ ደረጃውን ማላቅና እሱን ማክበርም ይገባል፡፡ እርሱ
የፈጣሪ ንግግር ነው፡፡ ከንግግሮች ሁሉ ትክክለኛውና በላጩ እርሱ ነው፡፡
• ምዕራፎቹንና አንቀፆቹን በማስተንተን እርሱን ዘወትር ማንበብ አለብን፡፡
የቁርኣንን ተግሳጻት፣ ዜናዎችና ታሪኮች ልናሰተነትን ይገባል፡፡ የሕይወታችንን
ደካማና ጠንካራ ጎን ለመለየት ሕይወታችንን ለቁርኣን መስጠት አለብን፡፡
• ድንጋጌዎቹን ልንከተል፣ ትዕዛዛቶቹንና ስርዓቶቹን
ልንተገብር፣ እንዲሁም የሕይወታችን መመሪያ
ልናደርገው ይገባል፡፡
እመት ዓኢሻ(ረ.ዐ)፣ ስለ ነብዩ (ስ.ዐ.ወ) ባህሪ
በተጠየቁ ጊዜ፣ «ባህሪያቸው ቁርዓን ነበር፡፡ « በማለት
መልሰዋል፡፡ (አህመድ 24601/ሙስሊም 746)
የሐዲሱ መልክት፣ ነቢዩ(ሰ.ዐ.ወ)፣ በኑሯቸውና በተግባራቸው የቁርዓንን
ድንጋጌና ሕግጋት በመፈፀም የሚያሳዩ እንደነበሩ ይገልጻል፡፡ በርግጥም ነብዩ
(ሰ.ዐ.ወ) ለቁርኣን መመሪያ ሙሉዕ ተከታይነታቸውን አስመስክረዋል፡
፡ እሳቸው ለእያንዳንዳችን ዓይነተኛ ተምሳሌታችን ናቸው፡
፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «ለናንተ አላህንና
የመጨረሻውን ቀን የሚከጅል ለኾነ ሰው አላህንም
በብዙ ለሚያወሳ፣ በአላህ መልክተኛ መልካም
መከተል አላችሁ፡፡» (አል አህዛብ 21)
> አንድ ሙስሊም ተውራትና ኢንጂል ከአላህ ዘንድ የተወረዱ እንደነበሩ ያምናል፡፡
ነገር ግን በርካታ ቅየራዎችና ድለዛዎች የተካሄደባቸው በመሆኑ ከቁርኣንና ከሱና ጋር
የሚጣጣመውን እንጂ በውስጣቸው ያለውን አንዱንም እውነት ብሎ አይቀበልም፡፡
በቀደምት መጽሐፍት ውስጥ ስላለ ነገር ሊኖረን የሚገባ አቋም
ምንድን ነው?
አንድ ሙስሊም፣ በነብዩላህ ሙሳ(ዐ.ሰ) ላይ የተወረደው
ተውራት፣ በነብዩላህ ዒሳ(ዐ.ሰ) ላይ የተወረደው ኢንጂል፣
በትክክል ከአላህ ዘንድ የተወረዱ እንደነበሩ ያምናል፡፡ ሁለቱም
በውስጣቸው ለሰው ልጆች ለዚች ዓለምና ለወዲያኛው ዓለም
ሕይወታቸው መመሪያና ብርሃን የያዙ፣ ተግሳጻትን እንዲሁም
ድንጋጌዎችንና ዜናዎችን አቅፈው የነበሩ መሆናቸውን ያምናል፡፡
ነገር ግን አላህ (ሱ.ወ) በቁርኣን ውስጥ የመጽሐፍት
ባለቤት የሆኑት አይሁዶችና ክርስቲያኖች፣ መጽሐፍታቸውን
እንደበረዙና እንዳበላሹ፣ ከመጽሐፍ ያልሆነን ነገር በውስጡ
እንደጨመሩ፣ ከነበረውም እንደቀነሱ ነግሮናል፡፡ በመሆኑም
በወረዱበት ይዘት ላይ አልቆዩም፡፡
አሁን ያለው ተውራት፣ በሙሳ(ዐ.ሰ) ላይ የተወረደው
ተውራት አይደለም፡፡ ምክንያቱም አይሁዶች አጣመውታል፤
ለውጠውታል፡፡ በርካታ ድንጋጌዎቹን ተጫውተውበታል፡፡ አላህ
(ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «ከነዚያ አይሁዳውያን ከሆኑት ሰዎች
ንግግሮችን ከስፍራዎቹ የሚያጣምሙ አሉ፡፡» (አል ኒሳእ 46)
አሁን ያለው ኢንጂልም ቢሆን
በዒሳ(ዐ.ሰ) ላይ የተወረደው
ኢንጂል አይደለም፡፡ ክርስቲያኖችም
ኢንጂልን አጣመውታል፡፡ በርካታ
በውስጡ የነበሩ ድንጋጌዎችን
ለውጠዋል፡፡ አላህ (ሱ.ወ)
ክርስቲያኖችን በማስመለከት
እንዲህ ብሏል፡- «ከነሱም
እርሱ ከመጽሐፉ ያላደለ ሲኾን
ከመጽሐፉ መኾኑን እንድታስቡ
በመጽሐፉ ምላሶቻቸውን
የሚያጣምሙ ክፍሎች አሉ፡፡
እርሱ ከአላህ ዘንድ ያልኾነ ሲኾን
እርሱ ከአላህ ዘንድ ነውም ይላሉ፡፡
እነርሱ የሚያውቁ ሲኾኑም በአላህ
ላይ ውሸትን ይናገራሉ፡፡» (አለ
ዒምራን 78)
«ከነዚያም እኛ ክርስቲያኖች ነን
ካሉት የጠበቀ ቃል ኪዳናቸውን
ያዝን፡፡ በርሱም ከታዘዙበት ነገር
ፈንታን ተዉ፤ ስለዚህ እስከ ትንሳኤ
ቀን ድረስ በመካከላቸው ጠብንና
ጥላቻን ጣልንባቸው አላህም
ይሰሩት የነበሩትን ሁሉ በእርግጥ
ይነግራቸዋል፡፡» (አል ማኢዳ 14)
ዛሬ በመጽሐፍት ባለቤቶች
እጅ የሚገኘው፣ ተውራትንና
ኢንጂልን አካቷል ብለው
የሚያምኑበት መጽሐፍ ቅዱስ፣
በውስጡ በርካታ ብለሹ የእምነት
አመለካከቶችንና ትክክለኛ ያልሆኑ
ዜናዎችን፣ እንዲሁም የውሸት
ትረካዎችን ይዟል፡፡ ስለሆነም
ከዚህ መጽሐፍ ውስጥ ቁርኣን
ወይም ትክክለኛ የሐዲስ ዘገባ
እውነትነቱን ያጸደቀውን በስተቀር
እውነት ብለን አናምንበትም፡
፡ ቁርኣንና ሀዲስ ያስተባበሉትን
ደግሞ እናስተባብላለን፡፡ ከዚህ ውጭ የሆነውን በዝምታ እናልፋለን፡፡ እውነት ብለን አናጸድቅም
ውሸት ነው ብለንም አናስተባብልም፡፡
እንዲህ ከመሆኑም ጋራ፣ አንድ ሙስሊም እነኚህን መጽሐፍት አያንኳስስም፤ አያራክስም፣
ምክንያቱም ምናልባት በውስጣቸው ያልተበረዘና ያልተለወጠ የአላህ ንግግር ቅሪት ሊኖር ይችላል፡፡
በመጽሐፍት የማመን ጥቅም ወይም ፍሬ
በመጽሐፍት ማመን በርካታ ጥቅሞች ወይም ፍሬዎች አሉት፡፡ ከነዚህ ጥቅሞች መካከል፡
አላህ (ሱ.ወ) ከምእመናን ላይ አደጋን በጠቅላላ ይመክታል፡፡ ከመከራና ስቃይ ውስጥ
ያወጣቸዋል፡፡ ከጠላቶቻቸው ሴራም ይጠብቃቸዋል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡-
«አላህ ከነዚያ ካመኑት ላይ ይከላከልላቸዋል፡፡» (አል-ሐጅ፡ 38)
አላህ በድንጋጌዎቹ ውስጥ ያለውን ጥበብ ወይም ምክንያታዊነት ማወቅ፡፡ ይኸውም ለያንዳንዱ
ሕዝብ ተጨባጭ ሁኔታውን የሚመጥንና ከባህሪው የሚስማማ የሆነ የራሱ ልዩ ድንጋጌ
የደነገገለት መሆኑ ነው፡፡ አላህ(ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «ከናንተ ለሁሉም ሕግንና መንገድን
አደረግን፡» (አል ማኢዳ 48)
እነኚህን መጽሐፍት በማውረድ ለተከሰተው የአላህ ጸጋ ምስጋና ማቅረብ፡፡ እነኚህ
መጽሐፍት በዱንያም በኣኺራም ብርሃንና መመሪያ ናቸው፡፡ ስለሆነም እያንዳንዳችን
ለዚህ ታላቅ የአላህ ጸጋ ምስጋና ማቅረብ ይጠበቅብናል፡፡
የሰው ልጅ መለኮታዊ መልዕክት ያስፈልገዋል፡፡
ለሰው ልጆች ሕግጋትን የሚያብራራላቸውና
ወደ ትክክለኛው ጎዳና የሚመራቸው ከጌታ የሆነ
መልዕክተኛ ሊኖራቸው የግድ ይላል፡፡ መለኮታዊ
መልዕክት የዓለም እስትንፋስና የሕይወት ብርሃን
ነው፡፡ መንፈስ፣ ሕይወትና ብርሃን የሌለው ዓለም
እንዴት ዓይነት ሕልውና ሊኖረው ይችላል?
አላህ (ሱ.ወ) መልክቱን ሩሕ ሲል የሰየመው ለዚህ
ነው ፡፡ ሩሕ ከሌለ ሕይወት የለም፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ
ብሏል፡- «እንደዚሁም ወደ አንተ ከትዕዛዛችን ሲኾን
መንፈስን (ቁርኣንን) አወረድን፡፡ መጽሐፉም እምነቱም
ምን እንደሆነ የምታውቅ አልነበርክም፡፡ ግን (መንፈሱን)
ከባሮቻችን የምንሻውን ሰው በርሱ የምንመራበት ብርሃን
አደረግነው፡፡ አንተም ወደ ቀጥተኛው መንገድ በርግጥ
ትመራለህ፡፡» (አል ሹራ 52)
ይኸውም የሰው ልጅ አዕምሮ በጥቅሉ
ጠቃሚና ጎጂ ነገሮችን መለየት የሚችል ቢሆንም፣
በመልዕክተኞች አማካይነት ካልሆነ በስተቀር
በረቀቀ መልኩ መጥፎውንና መልካሙን የሚለይበት
መንገድ አይኖረውም፡፡
> በመልዕክተኞች ማመን
በሁለቱም ዓለም ደስታም ሆነ ስኬት ሊገኝ የሚችልበት መንገድ በመልዕክተኞች እጅ የሚገኘው
ብቻ ነው፡፡ ክፉና ደጉንም በረቀቀ መልኩ የሚለየው መንገድ የነርሱ መንገድ ብቻ ነው፡፡ ለዚህ፣
መልዕክተኞች ካስተላለፉት መልዕክት ጀርባውን የሰጠ ሰው ለመልዕክቱ ተቃራኒ በሆነበትና
ጀርባውን በሰጠበት ልክ አለመረጋጋት፣ ጭንቀትና መረበሽ ያገኘዋል፡፡
በመልዕክተኞች ማመን ከኢማን ማዕዘናት መካከል አንዱ ነው፡፡
በመልዕክተኞች ማመን ከስድስቱ የኢማን ማዕዘናት መካከል አንዱ ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ
ብሏል፡- «መልዕክተኛው ከጌታው ወደ እርሱ በተወረደው አመነ፡፡ ምእመናንም (እንደዚሁ)፤
ሁሉም በአላህ፤ በመላዕክቱም፤ በመጽሐõፍቱም፣ ከመልዕክተኞቹ በአንድም መካከል አንለያይም
(የሚሉ ሲሆኑ ) አመኑ፡፡» (አልበቀራ 285)
አንቀጹ፣ በመልዕክተኞች መካከል ምንም ሳይለያዩ በሁሉም ማመን ግዴታ እንደሆነ ያስረዳል፡፡
አይሁዶችና ክርስቲያኖች እንዳደረጉት በከፊሎቹ አምነን በከፊሎቹ አንክድም፡፡
ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) የኢማን ማዕዘናትን አስመልክተው እንዲህ ብለዋል፡- «በአላህ በመላ በአላህ፣
በመጻሕፍቱ፣ በመልክተኞቹ፣ በመጨረሻው ቀንና በክፉም በደጉም በአላህ ውሳኔ ልታምን ነው፡፡»
(ሙስሊም 8)
በመልዕክተኞች የማመን ትርጓሜ
አላህ (ሱ.ወ) በእያንዳንዱ ሕዝብ ውስጥ ከነርሱው
የሆኑ፣ አላህን በብቸኝነት ወደ መገዛት የሚጣሩና ለርሱ
ተጋሪ እንደሌለው የሚያስተምሩ መልዕክተኞችን የላከ
መሆኑን በቁርጠኝነት ማረጋገጥ ነው፡፡ መልዕክተኞች
ሁሉም እውነተኞችና እውነተኝነታቸው በአምላክ
የተረጋገጠ ነው፡፡