መጣጥፎች

የመልዕክተኛው ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለምን ሱና ተግባራዊ ማድረግ ግዴታ ስለመሆኑና የተቃወመም ከሃዲ መሆኑን በተመለከተ


አዘጋጅ


የተከበሩ ሸይኽ


ዐብዱል ዐዚዝ ቢን ዐብደላህ ቢን ባዝ


አላህ ይዘንላቸውና


በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው


መቅድም


ምስጋና ሁሉ የአለማቱ ጌታ ለሆነው ለአላህ የተገባ ነው፤ መልካም ፍጻሜ ለጥንቁቆች ነው፤ የአላህ ውዳሴና ሰላም ለዓለማት እዝነት በመላው ባሮቹም ላይ ማስረጃ ሆነው በተላኩት የአላህ ባሪያና መልዕክተኛ ነቢያችን ሙሐመድ ላይ ይስፈን፣ በቤተሰቦቻቸውና እንዲሁም አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና በእነዚያ የተከበረውን ቁርኣን እና የነቢዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለምን ሱና ቃላቱንም መልዕክቱንም ከፍተኛና የተሟላ በሆነ አደራ ጠባቂነት ጠብቀው ለተተኪው ትውልድ ባስተላለፉት ባልደረቦቻቸውም ላይ የአላህ ውዳሴና ሰላሙ ይስፈን። እኛንም የእነርሱን ቅን ተከታዮች ያድርገን።


በመቀጠል፡


የጥንትም ሆኑ የዘመናችን ሊቃውንት በአንድ ድምጽ ከተስማሙባቸው ጉዳዮች መካከል ብይኖች የሚረጋገጡበት፣ የተፈቀዱና የተከለከሉ ጉዳዮችም የሚብራሩበት መሰረታዊ ምንጮች ከፊቱም ከኋላውም ስህተት በማይመጣበት በተከበረው ቁርኣን እና ከዚያም መለኮታዊ ራእይ (ወሕይ) ተገልጦላቸው እንጂ በስሜታቸው ከማይናገሩት የአላህ መልክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ፈለግ (ሱና) መሆናቸውን ነው። ከዚያም የሙስሊሙ ማህበረሰብ ሊቃውንቶች ስምምነትም እንዲሁ ማስረጃ ሲሆን፤ ከእነዚህ ውጪ ያሉትን የኢስላማዊ ምንጮች ፍርድን በተመለከተ በዋናነት ደግሞ ቂያስን አስመልክቶ በዑለሞች መካከል የሀሳብ ልዩነት አለ። ተገቢ ቅድመ መስፈርቶቹን ካሟላ ማስረጃ እንደሚሆን ታዲያ የብዙሃኑ ሊቃውንት እይታ ነው። እነዚህን መሰረቶች በተመለከተ የመጡት ማስረጃዎች ለቁጥርም አታካች ናቸው፤ መጠቀስም ከሚገባቸው በላይ የሚታወቁ ናቸው።


ሸሪዓዊ ድንጋጌዎችን በማፅናት ረገድ ታሳቢ የሚደረጉ መሰረቶች


የመጀመሪያው መሰረት፡ የአላህ ኪታብ


የመጀመሪያው መሰረት የአላህ ኪታብ (ቁርኣን) ነው።


ይህንን ኪታብ መከተል፣ አጥብቆ መያዝ እና ባስቀመጠው ገደብ ላይ መቆም ግዴታ መሆኑን የጌታችን ቃል የሆነው ቁርአን በተለያዩ ቦታዎች ጠቁሟል።


የላቀው አላህ እንዲህ ብሏል፡-


"ከጌታችሁ ወደእናንተ የተወረደውን ተከተሉ። ከአላህም ሌላ ረዳቶችን አትከተሉ። ጥቂትን ብቻ ትገሰጻላችሁ።"


የላቀው አላህ እንዲህ ብሏል፡-


"ይህም ያወረድነው የሆነ የተባረከ መፅሃፍ ነው ተከተሉትም ይታዘንላችሁ ዘንድ (ከክህደትም ) ተጠንቀቁ።"


የላቀው አላህ እንዲህ ብሏል፡-


"የመጽሀፉ ባለቤቶች ሆይ! ከመጽሀፉ ትሸሽጉት ከነበራችሁት ነገር ብዙውን ለእናንተ የሚገልጽ ከብዙውም የሚተው ሲሆን መልክተኛችን በእርግጥ መጣላችሁ። ከአላህ ዘንድ ብርሃን እና ገላጭ መጽሀፍ በእርግጥ መጣላችሁ።"


"አላህ ውዴታውን የተከተሉትን ሰዎች የሰላምን መንገዶች በእርሱ ይመራቸዋል። በፈቃዱም ከጨለማዎች ወደ ብርሃን ያወጣቸዋል። ወደ ቀጥተኛውም መንገድ ይመራቸዋል።"


የላቀው አላህ እንዲህም ብሏል፡-


"እነዚያ በቁርዐን እርሱ አሸናፊ መጽሀፍ ሲሆን በመጣላቸው ጊዜ የካዱት (ጠፊዎች ናቸው)።"


"ከኋላውም ከፊቱም ውሸት አይመጣበትም። ጥበበኛ ምስጉን ከሆነው ጌታ የተወረደ ነው።"


የላቀው አላህ እንዲህም ብሏል፡-


"ይህም ቁርኣን እናንተንና የደረሰውን ሰው ሁሉ በርሱ ላስፈራራበት ወደኔ ተወረደ።"


የላቀው አላህ እንዲህም ብሏል፡-


"ይህ (ቁርአን) ለሰዎች ገላጭ ነው። (ሊመከሩበት)፣ በእርሱም ሊስፈራሩበት"


ይህንኑ መልእክት የሚያንፀባርቁ የቁርአን አንቀጾች በርካታ ናቸው። ከመልዕክተኛውም ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ቁርኣንን አጥብቀን እንድንይዝ ከቁርአን ጋርም ትስስር እንዲኖረን ቁርኣንን የያዘ ቀጥተኛውን መንገድ የተመራ መሆኑን ችላ ያለው ደግሞ የጠመመ መሆኑን የሚጠቁሙ ሶሒሕ ሐዲሦችም በርከት ብለው የመጡበት ጉዳይ ነው።


ከእነዚህም መካከል ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም በመሰናበቻው ሐጅ ባደረጉት ኹጥባ ላይ እንዲህ ብለው የተናገሩት ተጠቃሽ ነው፦


"እኔ ከተከተላችሁትና አጥብቃችሁም ከያዛችሁት መቼም የማትሳሳቱበትና የማትጠሙበትን ነገር በመካከላችሁ ትቼላችኋለሁኝ፤ ይኸውም የአላህ ኪታብ ነው።"


ሙስሊም በሰሒሓቸው ዘግበውታል።


ከዘይድ ቢን አርቀም በተላለፈና ሙስሊምም በሶሒሓቸው በዘገቡት ሐዲሥ የአላህ መልዕክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል፦


"እኔ በመካከላችሁ ሁለት ከባባዶችን ትቻለሁኝ። የመጀመሪያው በውስጡ ብርሃንን እና ቀና ጎዳናን የያዘው የአላህ መጽሀፍ ነው። የአላህን መጽሀፍ አጥብቃችሁ ያዙት።"


የአላህን ቁርኣን አጥብቆ መያዝን እጅግ ካበረታቱ በኋላ ከዚያም እንዲህ አሉ፦


"ሌላኛው ቤተሰቦቼን ነው። ቤተሰቦቼን በተመለከተ አላህን አስቡ፤ ቤተሰቦቼን በተመለከተ አላህን አስቡ።"


በሌላ ዘገባም ስለቁርአን እንዲህ ብለዋል፦


እርሱ የአላህ ጠንካራው ገመድ ነው። በመሆኑም አጥብቆ የያዘው ሰው ቀጥተኛውን መንገድ ይዟል፤ እርሱን የተወ ሰው ደግሞ ጥመት ላይ ወድቋል።


ይህንን መልዕክት ይዘው የመጡ ሐዲሦች እጅግ በጣም ብዙ ናቸው። ከሶሓቦችም ከእነርሱ በኋላም የመጡት የእውቀት እና የኢማን ባለቤቶች የአላህን ኪታብ አጥብቆ መያዝ በርሱም መፍረድ እና ወደርሱም መዳኘት ግዴታ መሆኑ ላይ በሙሉ ድምፅ ከመስማማታቸው በተጨማሪ የመልዕክተኛው ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ሐዲሦች ታክሎበት የነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለምን ሱና አጥብቆ መያዝን በተመለከተ የመጡትን ማስረጃዎች ከመዘርዘር የሚያብቃቃ በቂና ፈዋሽ ማስረጃ እናገኝበታለን።


ሁለተኛው መሰረት፡- ከአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለምና ከባልደረቦቻቸው እንዲሁም ከነሱም በኋላ ከመጡት የእውቀትና የኢማን ባለቤቶች በጉዳዩ ተናግረውት ሶሒሕነቱ የተረጋገጠ ነው።


ሁለተኛውን መሰረት በተመለከተ፡- በአንድ ድምፅ ከተስማሙባቸው ሶስቱ መሰረቶች መካከል ሁለተኛው የአላህ መልእክተኛ፣ የነቢዩ ሶሓቦችና ከነሱም በኋላ ያሉት የእውቀትና የኢማን ባለቤቶች ተናግረውት ሶሒሕነቱ የተረጋገጠ ነው። ይህንን የመሰረቶች መሰረት አምነው የተቀበሉትና እንደ ማስረጃም የሚጠቀሙበት ህዝቡንም የሚያስተምሩት ነው። በርዕሰ ጉዳዩም ዙሪያ በርካታ መጽሃፎችን ጽፈውበታል። ይህንንም በኡሱል አል-ፊቅህ እና በሙስጠለሕ ኪታቦች ላይ አብራርተውታል። በዚህ ጉዳይ የመጡት ማስረጃዎች ስፍር ቁጥር የላቸውም። ከነዚህም መካከል እንድንከተለውና እንድንታዘዘው በአሸናፊው ቁርአን የተላለፈው ትእዛዝ ይጠቀሳል። ይኸውም በርሱ ጊዜ ለነበሩትም ከነሱ በኋላ ለሚመጡትም ሰዎች የሚመለከት ነው፤ ምክንያቱም የሳቸው መልዕክተኝነት ለሁሉም ነውና። ሰዓቲቱም እስክትመጣ ድረስ እንዲከተሉትና እንዲታዘዙት የታዘዙ በመሆናቸውም ነው። የአላህ መልዕክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም የአላህን ኪታብ የሚያብራሩና በውስጡ ያለውን ውበት በንግግራቸው፣ በተግባራቸውና በማፅደቃቸው ግልፅ የሚያደርጉ በመሆናቸውም ነው። ሱና ባይኖር ኖሮ ሙስሊሞች የሶላትን ረከዓ ብዛት፣ አሰጋገዱንና በውስጡ ያሉትን ግዴታዎች ባላወቁ ነበር። በፆም፣ በዘካ፣ በሐጅ፣ በጂሃድ፣ በመልካም ማዘዝንና ከመጥፎ መከልከልን በተመለከተ ያሉትን ፍርዶች በዝርዝር ባላወቁ ነበር። እንዲሁም በግብረገብነት ዙርያ የተቀመጡ ግዴታዎችንም ይሁን ክልከላዎችን መቀጣጫቸውንም በዝርዝር ባላወቁ ነበር።


በዚህ ረገድ ከመጡ የቁርአን አንቀፆች መካከል፦


በዚህ ረገድ ከመጡ የቁርአን አንቀፆች መካከል አላህ በሱረቱ ኣሊ‐ዒምራን ላይ እንዲህ ያለውን መጥቀስ ይቻላል፡-


"ይታዘንላችሁም ዘንድ አላህንና መልክተኛውን ታዘዙ።"


እንዲሁም የሁሉ የበላይ የሆነው አላህ በሱረቱ-ኒሳእ እንዲህ ያለውንም መጥቀስ ይቻላል፦


{እናንተ ያመናችሁ ሆይ! አላህን ተገዙ። መልክተኛውንና ከናንተም የስልጣን ባለቤቶችን ታዘዙ። በማንኛውም ነገር ብትከራከሩ በአላህና በመጨረሻው ቀን የምታምኑ ብትሆኑ (የተከራከራችሁበትን ነገር) ወደ አላህ እና ወደ መልክተኛው መልሱት። ይህ የተሻለ መጨረሻውም ያማረ ነው።}


የሁሉ የበላይ የሆነው አላህ በሱረቱ-ኒሳእ በድጋሚ እንዲህም ብሏል፦


{መልክተኛውን የሚታዘዝ ሰው በእርግጥ አላህን ታዘዘ። ከትእዛዝም የሸሸ ሰው (አያሳስብህ)። በእነሱ ላይ ጠባቂ አድርገን አልላክንህምና።}


የመልዕክተኛው ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ሱና ማስረጃም የሚሆን ሁሉም ደሞ የሚጠበቅ ካልሆነ በቀር እሳቸውን መታዘዙም ይሁን ሰዎች ያልተግባቡበትን ጉዳይ ወደ አላህ ኪታብ እና ወደ መልእክተኛው ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ሱና መመለስ እንዴት


ይቻላል? በናንተ አባባል ቢሆን አላህ ባሮቹን ወደ ሌለ ነገር ሂዱ ሲል አመላክቷል ማለት ይሆን ነበር። ይህ ደግሞ ከውሸትም ውሸትና በአላህ ላይ የሚደረግ ከባድ ክህደት እና በርሱም መጥፎ ጥርጣሬን ማሳደር ነው።


አሸናፊና የላቀ የሆነው አላህ በሱረቱ አን‐ነሕል እንዲህ ብሏል፡-


{ወደ አንተም ለሰዎች ወደነሱ የተወረደውን (ፍቺ) ልትገልጽላቸውና ያስተነትኑም ዘንድ ቁርኣንን አወረድን።}


በተጠቀሰው ሱራ እንዲህም ብሏል፦


{ባንተም ላይ መጽሀፉን አላወረድንም፤ ያንን በርሱ የተለያዩበትን ለነርሱ ልታብራራላቸውና ለሚያምኑትም ህዝቦች መሪና እዝነት ሊሆን እንጂ።}


አላህ ሱናቸው በሌለበት ወይም ምንም ማስረጃ ላይደረግ ነገር አንቀጹን እንዲያብራራ እንዴት መልዕክተኛውን ይወክላል?


የዚህ አምሳያውን የሁሉ የበላይ የሆነው አላህ በሱረቱል ኑር ላይም ተናግሯል፦


{አላህን ተገዙ። መልክተኛውንም ታዘዙ። ፤ ብትሸሹም(አትጎዱትም)። በእርሱ ላይ ያለበት የተገደደውን ማድረስ ብቻ ነው። ብትታዘዙትም ትምመራላችሁ። በመልክተኛውም ላይ ግልጽ ማድረስ እንጂ ሌላ የለበትም በላቸው።}


የበላይ የሆነው አላህ በዚሁ ምዕራፍ ላይ እንዲህም ብሏል፦


{ሶላትንም አስተካክላችሁ ስገዱ። ምጽዋትንም ስጡ። መልክተኛውንም ታዘዙ። ለእናንተ ሊታዘንላችሁ ይከጀላልና።}


በሱረቱል አዕራፍም እንዲህ ብሏል፦


{(ሙሐመድ ሆይ!) በላቸው፡- «እናንተ ሰዎች ሆይ! እኔ ወደናንተ ወደሁላችሁም የአላህ መልክተኛ ነኝ፡፡ (እርሱም) ያ የሰማያትና የምድር ንግሥና ለእርሱ ብቻ የኾነ ነው፡፡ እርሱ እንጂ ሌላ አምላክ የለም፡፡ ሕያው ያደርጋል፡፡ ይገድላልም፡፡ በአላህ በዚያም በአላህና በቃላቶቹ በሚያምነው የማይጽፍ የማያነብ ነቢይ በሆነው መልክተኛው እመኑ፡፡ ቅንንም መንገድ ትመሩ ዘንድ ተከተሉት።}


በእነዚህ አንቀጾች ውስጥ መመራት እና እዝነት እርሳቸውን ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም በመከተል የሚገኝ እንደሆነ ግልጽ ጥቆማ ይሰጣል። እናም የእርሳቸውን ሱና ባለመከተል ወይም ተቀባይነት የለውም ወይም አስተማማኝ አይደለም በማለት እንዴት እዝነት እና መመራት ሊገኝ ይችላል?


አሸናፊና ኃያል የሆነው አላህ በሱረቱ‐አን‐ኑር ላይም እንዲህ ብሏል፦


{እነዚያም ትዕዛዙን የሚጥሱ መከራ እንዳትደርስባቸው ወይም አሳማሚ ቅጣት እንዳያገኛቸው ይጠንቀቁ።}


በሱረቱል ሐሽር ላይም እንዲህ ብሏል፦


{መልክተኛውም የሰጣችሁን (ማንኛውንም) ነገር ያዙት። ከእርሱም የከለከላችሁን ነገር ተከልከሉ።}


ይህንኑ መልዕክት ይዘው የመጡ አንቀፆች እጅግ በርካታ ናቸው። ልክ ቀደም ብለን ቁርአንን መከተል፣ መመርያውን አጥብቆ በመያዝ ያዘዘውን መታዘዝ ክልከላውን መታቀብ ግዴታ መሆኑን እንደጠቆምነው እነዚህ ማስረጃዎችም የሚያመለክቱት እሳቸው ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ይዘውት የመጡትን መከተልና መታዘዝ ግዴታ መሆኑን ለመጠቆም ነው። እነዚህ ሁለቱ መሰረቶች ተዛማጅ ስለሆኑ አንዱን የካደ ሰው በሌላኛውም ክዷል አስተባብሏል። ይህ ደግሞ ክህደት፣ ጥመት እና ከእስልምና ምህዳር መውጣት መሆኑን የዒልምና የኢማን ሰዎች ዘንድ ስምምነት ያለበት ጉዳይ ነው።


በዚህ ጉዳይ ከረሱል ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ከመጡ ሐዲሦች መካከል፦


እሳቸውን ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም የመታዘዝ፣ ይዘውት የመጡትን የመከተል ግዴታና እርሳቸውን ማመፅን የሚከለክሉ የሓዲሥ ማስረጃዎች (በሙተዋቲር ደረጃ) እጅግ ተበራክተው የመጡበት ጉዳይ ነው። ይሀውም በሳቸው ጊዜ ለነበሩት እና ከሳቸውም በኋላ ላሉት ሁሉ እስከ ቂያማ ቀን ድረስ የሚዘልቅ ግዴታ ነው። ከነዚህም መካከል በቡኻሪና ሙስሊም በተዘገበው ከአቡ ሁረይራ (ረዲየላሁ ዐንሁ) በተላለፈው ሐዲስ ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል፡-


"የታዘዘኝ በርግጥ አላህን ታዟል፤ እኔን ያመፀ ደግሞ አላህን አምጿል።"


እንዲሁም በሰሂህ አል-ቡኻሪ ዘገባም ከአቡ ሁረይራ በተላለፈ ሓዲሥ ነቢዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል፡-


”ከእምቢተኞች በስተቀር ኡመቴ ሁሉ ጀነት ይገባሉ።” ባሉ ጊዜ “የአላህ መልእክተኛ ሆይ! (ጀነት ግባ ተብሎ) እምቢ የሚል ማን አለና?!” ተባሉ፤ እሳቸውም ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም፡- “እኔን የታዘዘ ጀነት ሲገባ አልታዘዝም ብሎ ያመፀ ደግሞ በርግጥ እምቢተኛ ሆኗል።” አሉ።


ኢማሙ አሕመድ፣ አቡ ዳውድ እና አል-ሐኪም በሰሒሕ ዘገባ ከአል-ሚቅዳም ኢብኑ መዕዲይ ከሪብ እንደዘገቡት የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል፦


"አዋጅ! እኔ ቁርአንንና አምሳያውን ተሰጥቻለው። አዋጅ! አንዳች ጥጋበኛ ሰው በአልጋው ላይ ተጋድሞ እንዲህ የሚልበት ጊዜም ይመጣል፡- “አደራ በዚሁ ቁርኣን ተብቃቁ። ሐላል ለመሆኑ በቁርአን ያገኛችሁትን (ብቻ) ሐላልነቱን ተቀበሉ፤ ሐራም ለመሆኑ በቁርአን ያገኛችሁትንም (ብቻ) ሐራምነቱን ተቀበሉ።”


አቡ ዳውድ እና ኢብኑ ማጃህ ሶሒሕ በሆነ ዘገባ ከኢብኑ አቢ ራፊዕ እንደዘገቡት የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል፦


"ይኽኔ አንዳችሁን በአልጋው ላይ ተጋድሞ እኔ ካዘዝኩባቸው መመርያዎች ወይንም ከከለከልኩት ክልከላዎች አንዳች ትእዛዝ ይመጣለትና እንዲህ ሲልም ላገኘው ይሆናል፦ “(ሓዲሥ የምትሉትን ነገር) አናውቅም! በቁርአን ካገኘነው ብቻ ነው የምንከተለው።”


ከሐሰን ቢን ጃቢር ረዲየላሁ ዐንሁ እንደተላለፈው ሚቅዳም ቢን መዕዲ ከሪብ አላህ መልካም ስራውን ይውደድለትና እንዲህ ሲል ሰምቻለሁ ብለዋል፦


የአላህ መልዕክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም በኸይበር ዘመቻ ቀን የተወሰኑ ነገሮችን ከለከሉና ከዚያም እንዲህ አሉ፡- “ከእናንተ መካከል አንዳችሁ ተጋድሞ ከኔ ሐዲሦች መካከል የሆነ ሐዲሥ እያወራ እንዲህ የሚልበት ጊዜ ይመጣል: ‘በኛና በናንተ መካከል የአላህ ኪታብ አለ። ሐላል የምንለው በቁርአን ሐላል ሆኖ ያገኘነውን (ብቻ) ነው። ሐራም የምንለውም በቁርአን ሐራም ሆኖ ያገኘነውን (ብቻ) ነው።’ አዋጅ! መልዕክተኛው የከለከለው አላህ እንደከለከለው ነው።"


ሐኪም፣ ቲርሚዚይ እና ኢብኑ ማጃህ ሶሒሕ በሆነ ዘገባ ዘግበውታል።


የአላህ መልዕክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም በኹጥባቸው ለባልደረቦቻቸው ያኔ በቦታው የተገኙት በቦታው ላልተገኙት እንዲያደርሱ ምክር በአደራ መልክ ያስተላልፉ እንደነበርና “ምናልባት መልክዕክቱ የሚደርሰው ከሰሚው ሰው የሚሻል ሆኖ ሊገኝ ይችላል።” ይሏቸውም እንደነበር ሐዲሶቹ (በሙተዋቲር ደረጃ) ተደጋግመው ተላልፈዋል።


ከነዚህም መካከል ነብዩ በአረፋ ቀን እና በየውመ ነሕር የመሰናበቻውን ኹጥባ በሚያደርጉበት ጊዜ በቡኻሪና ሙስሊም እንዲህ ማለታቸው ይገኛል፡-


"እዚህ የተገኘው እዚህ ላልተገኘ ያድርስለት፤ ምናልባት የተነገረው ከሰሚው የበለጠ የሚረዳው ሊሆን ይችላልና።"


የሳቸው ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ሱና በሰሚው ላይም ይሁን ከሰማ ሰው በደረሰው ላይም ሁሉ ማስረጃ የሚሆን፤ እስከ ትንሳኤ ቀን ድረስም የሚቀጥል ባይሆን ኖሮ የተገኙት ላልተገኙት እንዲያደርሱላቸው ባላዘዙ ነበር። በዚህም መሰረት የነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ሱና ከአንደበታቸው ለሰማውም ይሁን ከሰማ ሰው በትክክለኛ ዘገባ ለደረሰው ማስረጃ እንደሚሆንበት ግልፅ ሆነ።


የአላህ መልዕክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ባልደረቦችም የሳቸውን ቃላዊም ተግባራዊም ሱናቸውን በሚገባ ሐፍዘው (ጠብቀው) ከነሱ በኋላ ለመጡት ታቢዒዮች አስተላልፈዋል፤ ከዚያም ታቢዒዮቹም ከኋላቸው ለመጡት እንዲሁ አስተላልፈዋል። ልክ እንደዚሁ ታማኝ ሊቃውንት ከትውልድ ወደ ትውልድ እና ከዘመን ወደ ዘመን መቀባበሉን ቀጠሉበት። በመጽሐፎቻቸውም ውስጥ ሰብስበው ትክክለኛዎቹን ትክክል ካልሆኑት ለይተው ግልጽ አድርገዋል። በትክክል ከነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም የተገኘውን ሱና ትክክል ካልሆነው መለየት ያስችላቸውም ዘንድ በመካከላቸው የተግባቡበትን ሚዛን አደረጉ። የዒልም ባለቤቶችም የሱና ኪታቦችን ሁለቱ ሶሒሖችንም ጨምሮ ሌሎቹንም ሙሉ በሙሉ በሚገባ ተጠባብቀው ተቀባበሉት። ልክ የላቀው አላህ ኪታቡን ከቂሎች መጃጃል፣ ከጠማማዎች ጥመትና ከአበላሺዎች ማዛባት እንደጠበቀው ሁሉ፤ ከተከታዩ የቁርአን አንቀፅም መረዳት እንደሚቻለው፦


{ቁርኣኑን እኛ ነው ያወረድነው ፣ እኛ ለሱ ጠባቂዎች ነን።}


የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ሱናም ከአላህ የተወረደ ወሕይ ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም። አላህም የአጥፊዎችን ውዥንብር ይሁን የመሀይሞችን አተረጓጎም ውድቅ የሚያደርጉ፣ እንዲሁም አላዋቂዎች፣ ውሸታሞች እና ጠማማዎች በሱና ላይ የሚለጥፉትን ሁሉ የሚያስወግዱ አርቃቂ ዑለሞችንም መድቦላት ልክ ኪታቡን እንደጠበቀው ሁሉ የመልክተኛውንም ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ሱና ጠብቆታል። ምክንያቱም ጥራት የተገባው አላህ ለተከበረው ኪታቡ ትርጓሜ፤ በውስጧ ላሉ ጥቅል ፍርዶችም ማብራርያ እንዲሁም በተከበረው ቁርአን ላልተጠቀሱ ፍርዶች ማለትም ጡት በማጥባት የሚመጣ ዝምድናን እና አንዳንድ ውርስን የተመለከቱ ፍርዶች ማብራራትን ይመስል፣ ሴት ልጅን ከአባትዋ እህት ወይም ከእናቷ እህት ጋር አንድ ላይ ማግባት የተከለከለ መሆኑን እና ሌሎችም በትክክለኛ ሱና የመጡ ይሁን እንጅ በአላህ ኪታብ ውስጥ ያልተጠቀሱ መመርያዎችን ሁሉ የሚያጠቃልል ነው።


በዚህ ረገድ ከሶሓቦችና ከታቢዒዮች እንዲሁም ከነሱም በኋላ ከነበሩት ዑለሞች ከመጡት መካከል፡


ሱናን ማክበር እና በሱና የመስራት ግዴታነትን በተመለከተ ከሶሓቦችና ከታቢዒዮች እንዲሁም ከነሱም በኋላ ከነበሩት ዑለሞች የመጣውን እንጠቅሳለን።


በቡኻሪና ሙስሊም እንደተዘገበው አቡ ሁረይራ ረዲየላሁ ዐንሁ እንዲህ ብለዋል፦


የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ሲሞቱ እና ከዓረቦችም የካዱት በካዱ ጊዜ አቡበክር አስ-ሲዲቅ - አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና - እንዲህ አሉ፦


"በአላህ እምላለሁ! ዘካን ከሶላት የተለየች አድርገው የሚያዩ ካሉ እዋጋቸዋለሁ።"


ዑመርም ረዲየላሁ ዐንሁ እንዲህ አሉት፦


የአላህ መልክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለው ሳሉ እንዴት ትጋደላቸዋለህ፦


"ከአላህ በስተቀር ሌላ አምላክ የለም ብለው እስኪመሰክሩ ድረስ ህዝቡን እንድዋጋ ታዝዣለሁ፤ ይህንንም ባሉ ጊዜ በሌላ ሐቅ ካልሆነ በቀር ደማቸውና ንብረታቸው ከኔ የተጠበቀ ይሆናል።"


አቡበከርም ረዲየላሁ ዐንሁ እንዲህ አሉ፦


"ዘካህ (ደማቸውን ሓላል የሚያደርግ) ሐቅ አይደለምን?! በአላህ ይሁንብኝ! ለአላህ መልዕክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ሲከፍሉት የነበረን ግልገል እንኳ ቢከለክሉኝ እኔ በመከልከላቸው እዋጋቸዋለው።"


ዑመርም ረዲየላሁ ዐንሁ እንዲህ አሉ፦ "ልክ ያንኑ ሲለኝ ነበር በመፋለሙ ላይ የአቡበክርን ልቦና አላህ እንደከፈተላቸው የተገለፀልኝ፤ እውነት መሆኑንም ተረዳው።" ሶሓቦችም - አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና - አቡበክርን ደግፈው የተቀለበሱት ወደ እስልምና እስኪመለሱ ድረስ የካዱት ጋር ተዋጉ፤ በክህደቱ ላይ የጸኑትንም ገደሏቸው። ሱናን ማክበርና በሱና መስራት ግዴታ መሆኑ በዚህ ክስተት ውስጥ በግልፅ ጎልቶ ይስተዋላል። አንዲት አያት የውርስ ድርሻዋን ልትጠይቅ ወደ አቡበክር ረዲየሏሁ ዓንሁ መጣች፤ እሳቸውም እንዲህ አሏት፦ በአላህ ኪታብ ውስጥ ለአያት የተወሰነ ምንም ድርሻ የለም። የአላህ መልዕክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም በአያት ጉዳይ የወሰኑት ነገር ካለ የማውቀው ነገር የለምና ሰዎችን እጠይቃለሁ ብለው ከዚያም ሶሓቦችን በመጠየቅ የተወሰኑት ሶሓቦችም በቦታው ተገኝተው ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ለሴት አያት አንድ ስድስተኛ እንደሰጡ ሲመሰክሩላቸው አቡበክርም ለአያቲቱ አንድ ስድስተኛን ወሰኑላት። ዑመር ረዲየሏሁ ዐንሁ ሰራተኞቻቸው በሰዎች መካከል ሲፈርዱ በአላህ ኪታብ ተንተርሰው እንዲፈርዱ ጉዳዩን በአላህ ኪታብ ፍርድ ካላገኙለት ደግሞ በረሱል ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ሱና ተንተርሰው እንዲፈርዱ ይመክሯቸው ነበር። አንድ ሰው በአንዲት ሴት ላይ በፈጸመው በደል ምክንያት የሞተ ፅንስን ማስወረድ ያለውን ፍርድ በተመለከተም ሲጠየቁ ለመልሱ በተቸገሩ ጊዜ ስለጉዳዩ ሶሓቦችን አማከሩ። በቦታውም ሙሐመድ ቢን መስለማህ እና አል-ሙጊራህ ቢን ሹዕባህ ረዲየላሁ ዐንሁማ ተገኝተው ስለነበር ረሱል ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም በእንዲህ ዓይነት ጉዳይ ወንድ ወይም ሴት ባርያ ነፃ ማድረግን እንደወሰኑ ነገሯቸው። ዑመርም ረዲየሏሁ ዓንሁ በተመሳሳይ መልኩ ፍርድን ሰጡ።


ዑሥማንም ረዲየሏሁ ዓንሁ አንዲት ሴት ባሏ ከሞተ በኋላ በቤቷ ሆና ዒዳ መቁጠር ትችል እንደሁ በተጠየቁ ጊዜ የአቡ ሰዒድ ረዲየሏሁ ዓንሁ እህት ፉረይዓህ ቢንት ማሊክ ቢን ሲናን ረዲየላሁ ዐንሃ ባሏ ከሞተም በኋላ የተወሰነው የዒዳ ፍርድ እስኪጠናቀቅ ድረስ ዒዳዋን ባሏ ቤት ውስጥ እንደሆነች እንድትጨርስ ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዳዘዟት በነገረቻቸው ጊዜ ዑሥማን ረዲየላሁ ዓንሁ በተመሳሳይ መልኩ ፍርድ ሰጡ።


ልክ እንደዚሁ በነብያችን ሱና መሰረት በአል-ወሊድ ብን ዑቅባህ ላይ የአስካሪ መጠጥ መጠጣትን መቀጣጫ ወሰነ። ዑሥማን ረዲየላሁ ዓንሁ ሐጅ የሚያደርግ ሰው ተመቱዕ ማድረግ እንደሌለበት መናገራቸው ለዐልይ ረዲየላሁ ዓንሁ በደረሳቸውም ጊዜ ዓሊይ ረዲየላሁ ዐንሁ ሐጅና ዑምራን አንድ ላይ ነበር ያደረጉት። የመልዕክተኛው ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለምን ሱና ለማንም ቃል ብዬ የምተወው አይደለም። እንዲሁም አንዳንድ ሰዎች የሐጅ ሙትዓን በተመለከተ ኢብኑ ዓባስ ላይ ሐጅ መነጠል አለበት በሚለው የአቡበከር እና የዑመር ቃል ረዲየሏሁ ዐንሁማ ተንተርሰው በተቃወሟቸውም ጊዜ ኢብኑ አባስ እንዲህ ነበር ያሉት፦ "(በዚህ ሁኔታችሁ) ከሰማይ ላይ ድንጋይ እንዳይወርድባችሁ እሰጋለሁ፤ እኔ ረሱል ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል እያልኳችሁ እናንተ አቡበክር እና ዑመር ያሉትን ማስረጃ ታደርጉብኛላችሁን?!" በአቡበክር እና በዑመር ረዲየላሁ ዐንሁማ ቃል ተንተርሶ ሱናን መጣስ ለቅጣት ሊዳርግ የሚችል እንደሆነ ስጋት የሚጭር ከሆነ ከነሱ ውጭ በሆነ ንግግር ወይም በአስተያየቱ እና በኢጅቲሃዱ ብቻ ተንተርሶ የጣሰስ? አንዳንድ ሰዎች ዐብደላህ ቢን ዑመርን በአንዳንድ ሱናዎች ጉዳይ ላይ በጨቀጨቁት ጊዜ ዐብደላህም እንዲህ አላቸው፡- "እኛ ዑመርን እንድንከተል? ወይስ ሱናን እንድንከተል ነው የታዘዝነው?"


ዒምራን ቢን ሑሰይን ረዲየላሁ ዐንሁ ስለ ሐዲሥ እየተናገሩ ሳሉ ከመሀል የሆነ ሰው: “ስለቁርአን ንገረን” ሲላቸው ተናደዱና "ሱና የቁርአን ትርጓሜው (ተፍሲሩ) ነው፤ ሱና ባይኖር ኖሮ ዙሁር አራት፣ መግሪብ ሶስት፣ ሱብሒ ሁለት መሆኑንም ባላወቅን ነበር፤ የዘካ ዝርዝር ብያኔዎችንም ይሁን ሌሎች ሐዲሣዊ ዝርዝር ጉዳዮችንም ባላወቅናቸው ነበር።"


ከሶሓቦች - አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና - ለሱና (ለሓዲሥ) ከፍተኛ ቦታ መስጠት እና ሱናን ተግባራዊ ማድረግ ግዴታ መሆኑን እንዲሁም ሱናን ከመቃወም በማስጠንቀቅ ረገድ የተዘገቡት ዘገባዎች በጣም ብዙ ናቸው። እንዲሁም ዐብደላህ ቢን ዑመር - አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና - ተከታዩን የነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለምን ሐዲሥ ባወሩ ጊዜ፦ "የአላህ ሴት ባሮችን ከአላህ መስጊዶች አትከልክሏቸው።" ከልጆቹ አንዱ፡- "በአላህ እምላለሁ እንከለክላቸዋለን" አለ። ዐብደላህም እጅግ ተቆጥቶ ክፉኛ ስድብን ሰደበውና እንዲህም አለው፡- "እኔ ረሱል ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል እያልኩህ አንተ በአላህ እምላለሁ እንከለክላቸዋለን ትለኛለህ እንዴ?!" እንዲሁም ከአላህ መልዕክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ባልደረቦች አንዱ የሆነው ዐብደላህ ቢን አል-ሙገፈል አል-ሙዘኒይ - አላህ መልካም ስራውን ይውደድለትና - ከዘመዳቸው አንዱ ማንቲክ (የባላ ወንጭፍ) ሲወረውር በተመለከቱ ጊዜ ከለከሉት። እንዲህ አሉት፦ ነቢዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እሳቸው ማንቲክን ከልክለዋል። እንዲህም ብለዋል: 'ማንቲክ አደን ላያድን ጠላት ላይጎዳ፤ የሰው ጥርስ ይሰብራል ዓይንንም ያወጣል።' ከዚያም ድጋሚ ማንቲኩን ሲወረውር ባዩት ጊዜ እንዲህ አሉት፡- “በአላህ ይሁንብኝ! ከዚህ በኋላ አላናግርህም። የአላህ መልዕክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ማንቲክ እንደከለከሉ ነግሬህ አንተ ወደ ውርወራህ ትመለሳለህ?!”


አል-በይሀቂይ ታላቁ ታቢዒይ አዩብ አስ-ሰኽቲያኒ እንዲህ ማለታቸውን ዘግበዋል፦


ለአንድ ሰው ስለ ሱና ስትነግረው “ይህንን ተወውና እስኪ ስለ ቁርኣን ንገረን" ካለህ ይህ ሰው ጠማማ መሆኑን እወቅ።


አል-አውዛዒይም አላህ ይዘንላቸውና እንዲህ ብለዋል፡- “ሱና በቁርአን ላይ ዳኛ፤ ወይም ልቅ የተደረገውን የሚገድብ፤ ወይም ልክ ተከታዩን የአላህ ቃል ይመስል በቁርአን ውስጥ ያልተጠቀሱ ድንጋጌዎችን የሚደነግግ ነው፦


{ወደ አንተም ለሰዎች ወደነሱ የተወረደውን (ፍቺ) ልትገልጽላቸውና ያስተነትኑም ዘንድ ቁርኣንን አወረድን።}


እንዲህ ማለታቸውንም ቀደም ብለን አሳልፈናል፦


"አዋጅ! እኔ ቁርአንንና አምሳያውን ተሰጥቻለሁ።"


ዓምር አሽ-ሸዕቢይ ለአንዳንድ ሰዎች እንዲህ ማለታቸውን አል-በይሀቂይ ዘግበዋል፡- "እናንተ የጠመማችሁት (የቀደምቶችን) ፋና በተዋችሁ ጊዜ ነው።" ይህም ማለት ትክክለኛ ሐዲሶችን (በተዋችሁ ጊዜ) ማለት ነው። በተጨማሪ አል-አውዛዒይም ረሒመሁላህ ለተወሰኑ ባልደረቦቻቸው እንዲህ ማለታቸውን አል-በይሀቂይ ዘግበዋል፡ "የሆነ ሐዲሥ ከረሱል ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ከደረሰህ በሐዲሡ ከተባለው ሌላ ቃል ከማለት ተጠንቀቅ፤ ምክንያቱም የአላህ መልዕክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ከአላህ የተነገራቸውን ነውና እያደረሱ ያሉት።"


ታላቁ ኢማም ሱፍያን ቢን ሰዒድ አሥ-ሠውሪይም እንዲህ ማለታቸውን አል-በይሀቂይ ዘግበዋል፡- "ዒልም ሁሉ የነቢዩን ፈለግ ማወቅ ነው።"


ኢማም ማሊክም እንዲህ ብለዋል፡- "ከእኛ መካከል ሁሉም ቃሉ ይመልሳልም ይመለስበታልም የዚህ መቃብር ባለቤት ካልሆነ በቀር።" እያሉ ወደ ረሱል ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም መቃብር አመላከቱ።


አቡ ሓኒፋም አላህ ይዘንላቸውና እንዲህ ብለዋል፦


"ከረሱል ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ሐዲሥ ከመጣ በራስ እና በዓይን ነው የመጣብን (ከምንም በላይ ተቀዳሚ ነው)።"


ሻፍዒይም አላህ ይዘንላቸውና እንዲህ ብለዋል፦


"መቼም ቢሆን ከረሱል ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም የሆነ ትክክለኛ ሐዲሥ መጥቶልኝ ሳልከተለው ከቀረሁ አእምሮዬን ስቼ እንደሆነ ምስክር ሁኑልኝ።"


አላህ ይዘንላቸውና እንዲህም ብለዋል፦


"የሆነ ቃልን ተናግሬ የረሱል ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ሐዲሥ ደግሞ በተቃራኒው ሆኖ ከመጣላችሁ የኔውን ቃል ከአጥር ውጭ ወርውሩት።"


ኢማሙ አሕመድም አላህ ይዘንላቸውና ለተወሰኑ ባልደረቦቻቸው እንዲህ ብለዋል፦


"እኔንም በጭፍን አትከተሉ፤ ማሊክንም ይሁን አሽ-ሻፊዒይን በጭፍን አትከተሉ፤ ይልቁን እኛ ከወሰድንበት ምንጭ ውሰዱ።"


አላህ ይዘንላቸውና እንዲህም ብለዋል፦


"ከረሱል ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም የሆነ ትክክለኛ ሐዲሥ መጥቶላቸው ትክክለኛነቱንም እያወቁ ወደ ኢማም ሱፍያን የሚያደሉ ሰዎች ይደንቁኛል፤ ጥራት የተገባው አላህ `ኮ እንዲህ እያላቸው ነው፦


{እነዚያም ትዕዛዙን የሚጥሱ መከራ እንዳትደርስባቸው ወይም አሳማሚ ቅጣት እንዳያገኛቸው ይጠንቀቁ።}


"ፊትና ምን እንደሆነ ገብቶሀልን?" አሉና አስከትለው እንዲህ አሉ:


"ፊትና የተባለው ሺርክ ነው። ከነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም የሆነ ሓዲሥ ይመጣለትና አልቀበልም ብሎ ሲመልስ ያኔ በልቦናው ውስጥ መጥፎ ዝንባሌ ያድርበትና ሊቀሰፍ ይችላል።"


ታላቁ ታቢዒይ ሙጃሂድ ቢን ጀብርም ተከታዩን የአላህን ቃል በተመለከተ እንዲህ ማለታቸውን አል-በይሀቂይ ዘግበውታል፡-


"በማንኛውም ነገር ብትከራከሩ ወደ አላህ እና ወደ መልክተኛው መልሱት።"


"ወደ አላህ መመለስ ማለት ወደ ኪታቡ (ቁርኣን) መመለስ ሲሆን ወደ መልዕክተኛው መመለስ ማለት ደግሞ ወደ ሱናቸው መመለስ ማለት ነው።" ብለዋል።


አዝ-ዙህሪይ - አላህ ይዘንላቸውና - እንዲህ ማለታቸውንም አል-በይሀቂይ ዘግበዋል፦


ያለፉት ዑለማዎቻችን ሱናን በጥብቅ መከተል መዳን ነው ይሉ ነበር።


ሙወፈቁ-ድ-ዲን ቢን ቁዳማህ - አላህ ይዘንላቸውና - "ረውዳቱ-ን-ናዚር" በተሰኘው ኪታባቸው የአሕካም ኡሱሎችን (መሠረቶችን) በተመለከተ እንዲህ ብለዋል፡-


ሁለተኛው የማስረጃ መሰረት የረሱል ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ሱና ነው። የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ሐዲሥ ተአምራቸው ታማኝነታቸውን ያሳየ በመሆኑ፣ አላህም እንድንታዘዛቸው ያዘዘና እርሳቸውንም ከመቃረን ያስጠነቀቀን በመሆኑ ማስረጃ ነው።


የተፈለገው መልዕክት እዚህ ላይ አበቃ።


አል-ሐፊዝ ኢብኑ ከሢር አላህ ይዘንላቸውና ስለ ተከታዩ አንቀፅ ተፍሲር እንዲህ ብለዋል፡-


{እነዚያም ትዕዛዙን የሚጥሱ መከራ እንዳትደርስባቸው ወይም አሳማሚ ቅጣት እንዳያገኛቸው ይጠንቀቁ።}


ማለትም ከረሱል ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ትዕዛዝ በሌላ አገላለፅ አቋም፣ ህግጋት፣ መንገድ፣ ፈለግ፣ ድንጋጌ ውጭ የሆነ ማንኛውም ተግባርም ይሁን ቃል በረሱል ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ተግባርና ንግግር ይመዘናል፤ ገጥሞ ከተገኘ ንግግሩም ይሁን ተግባሩ ተቀባይነትን ያገኛል፤ ተቃርኖ ከተገኘ ደግሞ ማንም ይሁን ማን ቃሉም ተግባሩም አላህ ዘንድ ውድቅ ይሆናል።


በቡኻሪና ሙስሊም የሐዲሥ መዛግብት እንደሰፈረው የአላህ መልዕክተኛ - ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም - እንዲህ ማለታቸው ተዘግቧል፡-


"የኛ ጉዳይ (ትዕዛዝ) የሌለበትን ነገር የሰራ ሰዉ ወደርሱ ተመላሽ ነዉ።"


ማለትም በውስጥም ይሁን በግልጽ የረሱልን ህገ ደንብ የሚጻረር ሊሰጋና ሊጠነቀቅ ይገባዋል።


ፈተና እንዳይገጥማቸው


ማለትም በልቦናቸው ላይ ክህደት፣ ንፍቅና አልያም ቢድዐ እንዳይሰፍንባቸው።


ወይም አሳማሚ ቅጣት እንዳያገኛቸው


ማለትም በዱኒያ መገደል፣ መቀጣት፣ እስራት ወይም መሰል ስቃይ እንዳያገኛቸው።


ኢማሙ አሕመድ እንደዘገቡትና ዐብዱ-ር-ረዛቅ ከሙዐመር ቢን ሀማም ቢን ሙነበህ ሰምቻለሁ ብለው እንዳስተላለፉት እንዲህ ብለዋል፦


አቡ ሁረይራ እንዲህ ብለው ነግረውናል፦


የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል፦


"የኔ እና የናንተ ምሳሌው እሳትን እንዳቀጣጠለና ተመቻችቶም እንደተቀመጠ ሰው አምሳያ ነው። ያም ሰው እሳቱ ዙሪያውን ባበራለት ጊዜ እነዚህ የሳት እራት የሆኑት ነፍሳት እሳቱ ላይ መማገድ (ወደ እሳት ውስጥ መግባት) ጀመሩ፤ እርሱም እነሱን ማባረር ከእሳቱም መከልከሉን ቀጠለ። ይሁን እንጂ ነፍሳቱ ከእርሱ እያመለጡ መማገዳቸውን አላቆሙም። ይኸው ነው የኔ እና የእናንተ ምሳሌው፤ እኔ መታጠቂያችሁን ይዤ ከእሳቱ እመልሳችኋለው እናንተ ግን ከኔ እያመለጣችሁ ወደ እሳቱ ትማገዳላችሁ።"


ቡኻሪና ሙስሊም ከዐብዱረዛቅ ይዘው የዘገቡት ሐዲሥ ነው።


አስ-ሱዩጢይ -ረሒመሁላህ- “ሚፍታሑል ጀነቲ ፊል ኢሕቲጃጂ ቢሱነቲ” በተሰኘው ኪታባቸው እንዲህ ብለው አስፍረዋል፦


እወቁ አላህ ይዘንላችሁና የነብዩን ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ሐዲሥ ንግግርም ይሁን ድርጊት የታወቁት መሰረታዊ መስፈርቶቹ ከተሟሉ በኋላ ማስረጃ እንደሚሆን ያልተቀበለ ሰው ከሃዲ እና ከእስልምና ዳር ድንበር የወጣ ሰው ነው። ከሞት በኋላ መቀስቀሻውም ከአይሁዶችና ከክርስቲያኖች ወይም አላህ ከሻው የከሓዲያን ጭፍራ ጎራ ተሰልፎ ነው።


የተፈለገው መልዕክት እዚህ ላይ አበቃ።


ለሱና ከፍተኛ ቦታ መስጠትና በሱና መስራትም ግዴታ መሆኑን በማስመልከት እንዲሁም ሱናን ከመቃወም ማስጠንቀቃቸውን በሚመለከት ከሶሓቦች እና ከታቢዒዮች እንዲሁም ከነሱ በኋላም ከመጡት ዑለሞች የመጡ ማስረጃዎች እጅግ በጣም ብዙ ናቸው።


የጠቀስናቸው አንቀጾች፣ ሐዲሶችና ፋናዎች ላነሳነው ጉዳይ በቂ እና እውነትንም ለሚፈልግ ሰው አሳማኝ እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ።


አላህ እኛንም ሆነ ሙስሊሞችን ሁሉ እርሱ ለሚወደው ነገር እንዲገጥመን እና እርሱን ከሚያስቆጡ መንስኤዎችም እንዲጠብቀን ሁላችንንም ወደ ቀጥተኛው መንገድ እንዲመራንም እንለምነዋለን እርሱ ሰሚ እና ቅርብ ነውና።


የአላህ ውዳሴና ሰላም አገልጋይ ባርያው እና መልዕክተኛው በሆኑት ሙሐመድ በቤተሰቦቻቸው፣ በባልደረቦቻቸውና በቅን ተከታዮቻቸውም ሁሉ ይስፈን።


ዐብዱል ዐዚዝ ቢን ዐብደላህ ቢን ባዝ


አላህ ይዘንላቸው!


የመልዕክተኛው ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለምን ሱና ተግባራዊ ማድረግ ግዴታ ስለመሆኑና የተቃወመም ከሃዲ መሆኑን በተመለከተ


መቅድም


ሸሪዓዊ ድንጋጌዎችን በማፅናት ረገድ ታሳቢ የሚደረጉ መሰረቶች



የቅርብ ጊዜ ልጥፎች

መልእክት ከሙስሊም ሰባኪ ለክርስቲ ...

መልእክት ከሙስሊም ሰባኪ ለክርስቲያን ሰው

የሸዋል ስድስት ቀናት መፆም በጎነ ...

የሸዋል ስድስት ቀናት መፆም በጎነት SHAWAL

የተከበረው ቁርኣን ምንድን ነው? ...

የተከበረው ቁርኣን ምንድን ነው?

የመልዕክተኛው ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰ ...

የመልዕክተኛው ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለምን ሱና ተግባራዊ ማድረግ ግዴታ ስለመሆኑና የተቃወመም ከሃዲ መሆኑን በተመለከተ